1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሽብር ወንጀል ክስ የቀረበባቸው 51 ተከሳሾች ችሎት

ዓርብ፣ ሰኔ 9 2015

የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን ጨምሮ በእነ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ በፌደራል ዐቃቤ ሕግ በሽብር ወንጀል ክስ የቀረበባቸው 51 ተከሳሾች ሦስተኛ የችሎት ውሎ ተካሂዷል። ተከሳሾቹ የፖለቲካ እና የርዕዮት አላማን ለማራማድ በማሰብ የሽብር ድርጊት ፈጽመዋል በሚል በዐቃቤ ሕግ ክስ ቀርቦባቸዋል።

https://p.dw.com/p/4SglD
Symbolbild Justiz Indonesien
ምስል PantherMedia/picture alliance

የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን ጨምሮ በእነ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ በሽብር ወንጀል የተከሰሱ

የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን ጨምሮ በእነ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ በፌደራል ዐቃቤ ሕግ በሽብር ወንጀል ክስ የቀረበባቸው 51 ተከሳሾች ሦስተኛ የችሎት ውሎ ዛሬ ተደርጓል። ተከሳሾቹ የወንጀል ሕግ እንዲሁም የሽብር ወንጀልን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል ከወጣው አዋጅ ድንጋጌዎችን በመጣስ የፖለቲካ እና የርዕዮት አላማን ለማራማድ በማሰብ የሽብር ድርጊት ፈጽመዋል በሚል በዐቃቤ ሕግ ክስ ቀርቦባቸዋል።

ጉዳዩን የሚመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ የፀረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት በዛሬ ውሎው በሰነድ የቀረቡ ክሶች ከመዝገብ ቤት ተገቢው ማረጋገጫ ሰፍሮባቸው እንዲቀርቡ ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ተከሳሾች ደረሰብን ያሉትን ድብደባ ፣ ግርፋት እንዲሁም ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች በ15 ቀናት ውስጥ መርምሮና  አጣርቶ ውጤቱን ለችሎተ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ችሎቱ ዐቃቤ ሕግ በኤሌክትሮኒክስ ቁስ ( ፍላሽ ) አያይዞ ያቀረበውን ማስረጃ ተከሳሾች ማየት እንዲችሉ የአዲስ አበባ እና የፌዴራል ፖሊሶች መመልከቻ ኮምፒውተር እንዲያዘግልጁና ማስረጃውን የሚመለከቱበት በቂ ጊዜ እንዲመድቡም ከተከሳሾች የቀረበውን አቤቱታ ካደመጠ በኋላ ውሳኔ ሰጥቷል።

በዛሬው የችሎት ውሎ ከተከሳሾች መካከል የ67 ዓመት ግልሰብ ነኝ ያሉ ሰው ግርፋትና ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ፣ ሌላኛው ተከሳሽ ከተያዙ 77 ኛ ቀናቸው ቢሆንም የተፋጠነ ፍትሕ እያገኙ አለመሆኑን ፣ የፖለቲካ እሥረኞች ነን ብለው እንደሚያምኑ እና ችሎቱ ላይም የፖለቲካ ተጽዕኖ ሊኖር ይችላል የሚል ሥጋት እንዳላቸው ጠይቀዋል። ችሎቱ በበኩሉ ሙሉ የዳኝነት ነፃነት እንዳለውና ተከሳሾች በዚህ ጉዳይ ላይ ሥጋት እንዳይገባቸው በማሳሰብ በቀረቡ አቤቱታዎች ላይ ብይን ለመስማት ለሰኔ 15 ቀን 2015 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል።

ይህ ጉዳይ ላይ ለ ሦስተኛ ጊዜ የተሰየመው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ የፀረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት ከተከሳሾች ለተነሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ምርመራ አድርጎ ውጤቱን ለችሎቱ ይዞ እንዲቀርብ፣ በቀረበው ክስ ላይ ክሱን ያቀረበው ዐቃቤ ሕግ የክስ ሰነዱ ላይ ስም፣ ፊርማ እና ማህተም ስላልነበረው ይህ ተስተካክሎ እንዲቀርብ በቀረበው አቤቱታ ላይም ብይን ለመስጠት ነበር ለዛሬ ቀጠሮ የተያዘው። ይሁንና የመሀል ዳኛው ሀዘን ስለገጠማቸው የተሰጠው ብይን የግድ ዳኛው ባሉበት መነበብ ስለነበረበት በሚቀጥለው የችሎቱ ውሎ እንዲቀርብ ችሎቱ ወስኗል። ይህንን ተከትሎ ችሎቱ  ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን ተመልክቷል። በዚህም ተከሳሾች በችሎቱ ባሰሙት አቤቱታ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መርማሪዎች ተከሳሾች ደረሰብን የሚሉትን አቤቱታ ሲያቀርቡ ፖሊስ አብሮ በመሆን በነፃነት እንዳይናገሩ እንቅፋት እየሆነባቸው መሆኑን አስረድተዋል።

የ67 ዓመት ሰው መሆናቸውን የገልፁ ተከሳሽ የልጅ ልጃቸው በሚሆን ወጣት የፖሊስ አባል ግርፋት እና ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ለችሎቱ አቤቱታ አቅርበዋል። የሰብዓዊ ምርመራ ሪፖርቱን ለችሎቱ ዛሬ ማቅረብ ያልቻለው የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የምርመራ ቡድን ተደራራቢ ሥራ በመኖሩ ያንን ማድረግ እንዳልቻለ ገልጾ በቀጣይ ሥራውን በታዘዘው መሰረት እንደሚፈጽም አስታውቃል።

ችሎቱም የምርመራ ቡድኑ ሥራውን ለመሥራት የሚቸገርበት ሁኔታ ካለ እና የሚደርስበት ጫና ካለ ለችሎቱ እንዲያስረዳ በማሳሰብ የተከሳሾችን የመብት ጉዳዮች መርምሮ ለሰኔ 23 ይዞ እንዲቀርብ ራሱን ችሎ ቀጠሮ ተሰጥቶታል። ሌላኛው ተከሳሽ ለችሎቱ ባሰሙት አቤቱታ "እኛ የፖለቲካ እሥረኞች ነን ብለን የምናምን ሰዎች ነን። ችሎቱ ላይም የፖለቲካ ተጽእኖ ይኖራል ብለን የምናምን ሰዎች ነን" በማለት በፍላሽ የቀረበባቸውን ማስረጃ የታሰሩበት ቦታ ይዘው እንዳይገቡ እና እንዳይመለከቱ ፖሊሶች "ከበላይ ትእዛዝ የመጣ ነው" በሚል ክልከላ እያደረጉባቸው መሆኑን ተናግረዋል። በድምፅ የቀረበብን ማስረጃ "የተቀናበረ ሊሆን ስለሚችል" በትክክል ማድመጥ ስላለብን እንዲሁም ከጠበቆቻችን ጋርም በቂ የመነጋገሪያ ጊዜ እንዲሰጠን የሚሉ ጥያቄዎች ተደጋግመው ከተከሳሾች ቀርበዋል።

በሌላ በኩል "በዜግነታችን ብቻ አስቸኳይ ፍትሕ ይሰጠን" ያሉ ተከሳሽ መንግሥት ያሰረን በሀገሪቱ ውስጥ እየተስተናገዱ ያሉ ጉልህ የፖለቲካ ሁኔታዎች እና ውሳኔዎች ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዳይኖረን ለማድረግ ነውና ይህንን ችሎቱ ይመልከትልን የሚሉ ጥያቄዎች ቀርበዋል። ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ የቀረቡትን የመብት ጥያቄዎች እንደሚቀበላቸው ገልጾ ሆኖም ግን በፍላሽ የቀረበው ማስረጃ ላይ ከመከራከራችን በፊት በቅድሚያ ክስ ይሰማ ፣ ከዚያ በኋላ በቁሱ ውስጥ ያለውን ማስረጃ መስማት ይሻላል ብሎ ተከራክሯል። አክሎም የአዲስ አበባም ይሁን የፌዴራል ፖሊስ ማረሚያ ቤቶች በፍላሽ የቀረበውን ማስረጃ መመልከቻ ቦታ እንደሌላቸው ጠቅሶ ተከራክራል።

ፖሊስ በበኩሉ ተከሳሾች የክስ ማስረጃ የተሰነደበትን ፍላሽ ወደታሰሩበት ቦታ ይዘው እንዳይገቡ መከልከሉን ለችሎቱ አምኗል። ፖሊስ ያንን ያደረገው ማንኛውም የኤሌክትሮኒክስ ቁስ ወደ ግቢው እንደማይገባ የተቋም ደንብ ስለሚከለክል ነው ቢልም ተከሳሾች ግን ይህ ክልከላ የተጣለብን ከበላይ ሥራ አሥፈፃሚዎች ለፖሊስ በስልክ ተደውሎ በመታዘዙ ነው ብለው ተከራክረዋል። ይሁንና ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ከሰጠ ፖሊስ ያንን ሥራ የማስፈፀም ግዴታውን እንደሚወጣ ለችሎቱ አረጋግጧል።

የግራ ቀኙን ክርክር እና ሀሳብ ያደመጠው በሦስት ዳኞች የተሰየመው ችሎቱ ተከሳሾች በክስ ማስረጃነት የቀረበውን ፍላሽ የማየት ሙሉ መብት እንዳላቸው ትእዛዝ ሰጥቷል። ፖሊስም ሆነ ሌሎች ተቋማት ተከሳሾቹ ማስረጃዎቹን እንዲያዩ እንዲያመቻቹ ፣ ኮምፒውተር ጭምር እንዲያዘጋጁ ብሎም በቂ የመመልከቻ ጊዜ እንዲመቻችላቸው ጥብቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ከችሎቱ የዳኝነት ነፃነት ጋር ተያይዞ ለቀረበው ጥያቄም ችሎቱ "ከነፃነት ጋር በተገናኘ ሥጋት ሊገባችሁ አይገባም፣ ሥራችንን በነፃነት እንሠራለን" ሲል ማሳሰቢያም ፣ ማረጋገጫም ሰጥቷል። 51 ዱ ተከሳሾች ስለቀረበባቸው የክስ ጭብጥ ከጠበቆቻቸው መካከል አንዱ የሆኑትን ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝን ጠይቀናቸዋል። "ሽብር ነው። ሽብር ምንድን ነው መንግሥትን በመገልበጥ ሌላ መንግሥትን ለመመስረት የተደረገ ዝግጅት እና እቅድም አለ እንዲሁም ያንን ለማድረግ ተባብረዋል በሚል ነው" በማለት መልሰዋል።

ይህንን የክስ ጉዳይ የያዘው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ የፀረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት በዛሬ ውሎው አንድ ተከሳሽ ውክልና ለመስጠት ያቀረቡትን ጥያቄ በመቀበል ተከሳሹ ውልና መስረጃ መቅረብ እንዲችሉ ፖሊስ እጀባ እንዲያደርግላቸው፣ ሁለት የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን የሚመሩ ተከሳሾች ደግሞ በድርጅቶቹ እርዳታ የሚደረግላቸው ሰዎች እንዳይጎዱ ቸክ የመፈረም መብታቸው እንዲከበርላቸው፣ ፖሊስ ያንን እንዲያስፈጽም ትዕዛዝ ሰጥቷል።  ችሎቱ ቀጣይ ጉዳዮችን ለመመልከት ለቀጣይ ሀሙስ ለሰኔ 15 ቀን 2015 ዓ. ም ቀጠሮ ሰጥቷል።

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

ታምራት ዲንሳ