1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሱዳን ጦርነቱን ለማቆም ፈቃደኝነት መጥፋቱ

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 8 2015

ከሚያዝያ ወር ጀምሮ የሱዳን ሠራዊት አዛዥ አብዱልፈታህ አል ቡርሃን እና ተቀናቃኛቸው የፈጥኖ ደራሹ ኃይል (RSF) መሪ ሄሜቲ በመባል የሚታወቁት መሀመድ አምዳን ዳጋሎ ሥልጣን ለመያዝ እየተዋጉ ነው። እስካሁን ሁኔታውን አረጋግቶ ውጊያውን ለማስቆም የተደረገው ጥረት አልተሳካም። የተኩስ አቁም ስምምነቶችም በተዳደጋጋሚ ተጥሰዋል።

https://p.dw.com/p/4Tw8I
Egypt launches fresh Sudan mediation attempt at summit
ምስል Ibrahim Mohammed Ishak/REUTERS

የሱዳን ቀውስ

 

ሱዳን ውስጥ የተጠናከረው ጥቃት የሕዝቡን ችግር አባብሶታል። ሰብአዊ ቀውሱንም አስከፊ አድርጎታል ትላለች የዶቼቬለዋ ማርቲና ሽቪኮቭስኪ። በሱዳን መንግሥት ጦር እና በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (RSF) መካከል ከሦስት ወራት በላይ ያስቆጠረው ከባድ ውጊያ ተጠናክሮ መቀጠሉን የፖለቲካ ተንታኙ አህመድ ሱሌማን ከዶቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አመልክተዋል። «አስከፊው ውጊያ በኻርቱም እና በአጎራባች ከተሞች እንዲሁም በዳርፉር በመካሄድ ላይ ነው» የሚሉት ሱሌማን በዚህም የመሠረተ ልማቱ እየወደመ መሆኑን፤ ስደተኞች የተጠለሉበት ለጉዳት መዳረጉን እንዲሁም ከፍተኛ መፈናቀል እና የከፋ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እየተፈጸመ እንደሚገኝም የለንደኑ ቻተም ሀውስ የአፍሪቃ ቀንድ ጉዳይ ተመራማሪው ያስረዳሉ።  በአጭር ጊዜ ውስጥ በተካሄደው ውጊያም ከሦስት ሚሊየን በላይ ሕዝብ ለመፈናቀል መገደዱን የተመድ የገለጸ ሲሆን የሞቱትም ከአንድ ሺህ በላይ እንደሚገመቱ ነው ይፋ ያደረገው። የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን UNHCR «ሁሉን ያካተተ የእርስ በእርስ ጦርነት» ሊከተል እንደሚችል በማመልከትም፤ ሁኔታው አጠቃላይ አካባቢውን ወዳለመረገጋጋት ሊከተው እንደሚችልም አስጠንቅቋል።  

Egypt Sudan Conflict Summit
በግብፅ የተካሄደው የሱዳን ሰላም ውይይትምስል Egypt's presidency media office/AP/picture alliance

ከሚያዝያ ወር ጀምሮ የሱዳን ሠራዊት አዛዥ አብዱልፈታህ አል ቡርሃን እና ተቀናቃኛቸው የፈጥኖ ደራሹ ኃይል (RSF) መሪ ሄሜቲ በመባል የሚታወቁት መሀመድ አምዳን ዳጋሎ ሥልጣን ለመያዝ እየተዋጉ ነው። እስካሁን ሁኔታውን አረጋግቶ ውጊያውን ለማስቆም የተደረገው ጥረት አልተሳካም። በሁለቱ ወገኖች መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት በተደጋጋሚ ፈርሷል፤  በተቀናቃኝ ኃይሎቹ መካከል የሚካሄደው ከፍተኛ ውጊያም ለተረጋጉ ስምምነቶች ቦታ አልሰጡም፤ እስካሁን የተደረጉ የሽምግልና ሙከራዎችም ውጤት አላመጡም ይላሉ የፖለቲካ ተንታኙ አህመድ ሱሌማን።

«እስካሁን የተደረጉ የሽምግልና ሙከራዎች እምብዛም ውጤታማ አልሆኑም፤ በሳውዲ እና ዩናይትድ ስቴትስ አማካኝነት የተሞከረውን አይተናል፤ የተኩስ አቁም ስምምነት በማረጋገጥ የሰብአዊ እርዳታ እንዲገባ የማድረግ ጥረት ነበር፤ የታየው ግን ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች በምንም መልኩ ቢሆን ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተው ጦርነቱን ከማቆም ይልቅ ስልታዊ በሆነ መልኩ አንዳቸው ሌላቸው ላይ ጫና ለማድረግ መሞከራቸውን አይተናል።»

Suadan | General Abdel Fattah al-Burhan in Khartum
ጀነራል አብደል ፈታል አልቡርሃን ኻርቱም ከወታደሮች ጋርምስል Sudanese Armed Forces/AA/picture alliance

በዚህ ሳምንት ሰኞ ዕለት የምሥራቅ አፍሪቃ በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) በኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ላይ የሱዳን ሰላም ጉባኤ አካሂዷል። አልቡርሃንም ሆኑ ዳጋሎ ግን በጉባኤው አልተገኙም። ቢያንስ RSF ወኪሉ በጉባኤው እንዲሳተፍ የላከ ሲሆን የሱዳን መንግሥት ግን ኬንያ ቡድኑን ትደግፋለች በሚል ከሰብሳቢነት ካልተነሳች በቀር በኢጋድ ጉባኤ እንደማይገኝ አሳውቋል። የሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ኬንያን ለRSF ሚሊሺያዎች ስልጠና እና የተለያዩ ድጋፎች በመስጠትም ከሷል። በተጨማሪም ቀደም ሲል በግንቦት ወር ቻድ እና ሳውድ አረቢያ ላይ የተካሄዱ የሰላም ጥረቶች አልቦ ውጤት ቀርተዋል። ከዚህ በመነሳትም የቻተም ሀውስ የአፍሪቃ ቀንድ ጉዳይ ተመራማሪው አህመድ ሱሌይማን ተዋጊዎቹ ኃይላት ስልታዊ ወታደራዊ ስኬት ማግኘት ላይ ማተኮራቸውን ይናገራሉ።

የፈጥኖ ደራሹ ኃይል መሪ የሀምዳን ዳጋሎ የፖለቲካ አማካሪ የሆኑት ዩሱፍ ኢዛት ግን በዚህ ፈጽሞ አይስማሙም። እንደውም ሌላኛውን ወገን ለድርድር የቀረቡትን ሃሳቦች ባለመቀበል ይከሳሉ። ኢዛት ከዶቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ በቅድሚያ የችግሩን ሥረ መሠረት ማወቅ ይገባል ነው ያሉት።

IGAD Treffen / Sudan in Addis Abeba
አዲስ አበባ ላይ ኢጋድ ያካሄደው የሱዳን ሰላም ጉባኤምስል Office of the PM Ethiopia

«ሱዳን ውስጥ ያለውን ጦርነት መነሻ መሠረታዊ ምክንያቶች መነጋገር ያስፈልጋል። አንድ ብሔራዊ ጦር መገንባት ይኖርብናል፤ ከፖሊሶዎች ጋር ስለአዲሲቱ ሀገር መስማማት አለብን፤ ሱዳንን ጨምረን ሁሉንም ተቋማት መልሰን ማቋቋም አለብን፤ ለሀገሪቱ ፌደራል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማምጣት አለብን፤ ይህንን ነው መወያየት የምንፈልገው። ጉዳዩ የግል እና በሁለት ጀነራሎች መካከል የሆነ ነገር አይደለም፤ ጉዳዩ በRSF እና በሱዳን ጦር ኃይል መካከልም የሆነ አይደለም፤ የሚመለከተው የፖለቲካ እና ዴሞክራሲዊ ሽግግሩን የሚደግፉ ሁሉንም ሱዳናውያን ነው።»

በአንድ ወቅት አል ቡርሃን እና የቀድሞው ምክትላቸው ዳጋሎ በጋራ ቆመው ነበር። በጎርጎሪዮሳዊው 2019 ዓ,ም በተካሄደው ሕዝባዊ ተቃውሞ ለረዥም ዓመታት ሀገሪቱን የገዙትን ኦማልር አልበሽርን ከሥልጣን አወረዱ። ከዚያም ብዙም ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ በፊት ሁለቱም የተሳተፉት ሌላ መፈንቅለ መንግሥት ተከተለ። እንደ ዳጋሎ የፖለቲካ አማሪ ኢዛት ገለጻ ከሆነም ግጭቱ የሚያጠነጥነው ለፖለቲካ ሂደቱ ድጋፍ በሚሹ፣ የዴሞክራሲያዊ ሽግግር በሚፈልጉ እና የቀድሞውን ሥርዓት መመለስ በሚፈልጉ እንዲሁም በእስላማዊ ጽንፈኞች ላይ ነው። እንደእሳቸው እምነት ሱዳን ነጻ የምትወጣበት ጊዜ አሁን ነው። አዲስ አቅጣጫም መያዝ አለባትም ባይናቸው። ሽብርተኛ ያሉት ጽንፈኛ ኃይል ዳግም አቅም ኖሯቸው እንዲመለሱ አይፈልጉም። ሄሜቲ የሚሏቸው የRSF መሪ ዳጋሎ የሚታገሉት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመትከል እንደሆነም ይሟገታሉ።

People watch as smoke rises during clashes between the army and the paramilitary Rapid Support Forces (RSF), in Omdurman
በተቀናቃኞቹ ኃይሎች ውጊያ የተጨነቁት የሱዳን ወጣቶች ምስል Mostafa Saied/REUTERS

«ሄሜቲ የሚዋጉት ለራሳቸው ሀገሩን ለመምራት በመፈለግ አይደለም። በፍጹም፤ ጦርነቱ የተጀመረው እሳቸው እና RSF ዴሞክራሲያዊ ሂደቱን ስለሚደግፉ ነው። እንዲሁም ሲቪሎችን በመ,ደገፍ ሀገሪቱን በሽግግር መንገድ ማለፏን ስለሚደግፉ ነው። ለዚህም ነው ሄሜቲ ላይ አነጣጥረው የሚያጠቁት። እናም አሁን ሄሜቲ የሚያምኑት ችግሩን ማስወገጃው ብቸኛው መንገድ፣ አምባገነን መንግሥት ለማምጣት ወይም እራሳቸው መሪ ለመሆን አይደለም፤ አንዳችን ሌላችንን እንድንቀበል፣ ፍትህ እኩልነትን የሚያሰፍን፤ ብዝሃነትን አምኖ ችግር ለመፍታት የሁሉንም ሱዳናውን ማንነት መቀበል የሚያስችል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመሥረት ነው። ይኽነው፤ የግል ጉዳይ አይደለም።»

FILE PHOTO: Lieutenant General Mohamed Hamdan Dagalo greets his supporters as he arrives at a meeting in Aprag village
የፈጥኖ ደራሹ ኃይል መሪ ሃምዳን ዳጋሎምስል Umit Bektas/REUTERS

ሱዳንን ከፖለቲካው ውጥረት ወደጦርነት የከተታት መነሻ  ምክንያት ግን አሁንም እያነጋገረ ነው። ዶቼ ቬለ የሱዳን መንግሥት ቃል አቀባይን በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም። እንዲያም ሆኖ ሱዳን ውስጥ አሁንም ውጊያው መቀጠሉን ከስፍራው የሚወጡ ዘገባዎች ያሳያሉ። ሱዳንን ከገባችበት ቀውስ ለማውጣት በግብፅ ሰብሳቢነት አገራባች ሃገራት ትናንት ካይሮ ላይ ተገናኝተው በመምከር የመፍትሄ ሃሳብ ያሉትን በበኩላቸው አቅርበዋል። የኢትዮጵያን ጨምሮ፤ የኤርትራ፣ የደቡብ ሱዳን፣ የቻድ፣ የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ እንዲሁም የሊቢያ መሪዎች፣ የሱዳን ጀነራሎች የለኮሱትን ግጭት ጦርነት ባስቸኳይ እንዲያቆሙ ጠይቀዋል። የግብፅ ፕሬዝደንት አብደል ፋታህ አልሲሲ ተፋላሚ ኃይላት የሰብአዎ እርዳታ የሚገባበትን ደህንነቱ የተረጋገጠ መንገድ እንዲከፍቱም አሳስበዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ