1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በለገደንቢ ወርቅ ማውጫ የጤና እክል እያስከተለ ነው የተባለው ብክለት

ዓርብ፣ ሚያዝያ 20 2015

በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ኦዶ ሻኪሶ ወረዳ በለገደንቢ ወርቅ ማውጫ የተሰማሩ ኩባንያዎች ለአከባቢ ጥበቃ አነስተኛ ትኩረት መስጠታቸው በማኅበረሰቡ ላይ የጤና እክል እያስከተለ መሆኑን ሂዩማን ራይትስ ዎች አመልክቷል። የአከባቢው ማኅበረሰብ አባላትም በኬሚካሎች ምክንያት ከፍተኛ የጤና ጠንቅ የሆኑ ጫናዎች እየተከሰቱ መሆኑን ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/4QgTc
Human Rights Watch Logo Flash-Galerie
ምስል Human Rights Watch

በለገደንቢ ወርቅ ማውጫ የጤና እክል

በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ኦዶ ሻኪሶ ወረዳ በለገደንቢ ወርቅ ማውጫ የተሰማሩ ኩባንያዎች ለአከባቢ ጥበቃ አነስተኛ ትኩረት መስጠታቸው በማኅበረሰቡ ላይ የጤና እክል እያስከተለ መሆኑን ሂዩማን ራይትስ ዎች አመልክቷል። የአከባቢው ማኅበረሰብ አባላትም በወርቅ ማውጫው ሂደት ጥቅም ላይ በሚውሉ ኬሚካሎች ምክንያት ከፍተኛ የጤና ጠንቅ የሆኑ ጫናዎች እየተከሰቱ መሆኑን ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። ገመዳ ጤጤ በጉጂ ዞን የኦዶ ሻኪሶ ወረዳ ነዋሪ ሲሆኑ በለገደምቢ ማዕድን ማውጫ አካባቢ በነዋሪዎች ላይ ያደርሳል በሚባለው የጤና እክል ተጎጂ ከሆኑ ቤተሰቦች አንዱ መሆናቸውን ያስረዳሉ። የ12 ዓመት አዳጊ ልጃቸው በለገደንቢ ወርቅ ማውጫ ጥቅም ላይ በሚውለው ኬሚካል ምክንያት ለአካል ጉዳት ተዳርጋ ተንቀሳቅሳ ምንም ማድረግ እንደተሳናትም ይገልጻሉ። ከወርቅ ማምረቻው የሚወጣው ንጥረነገር እንዲሁ በሜዳ ላይ መለቀቅ መቀጠሉን የተናገሩት እኚህ ነዋሪ፤ ልጃቸውም የዚሁ ሰለባ በመሆኗ ገና ከሁለት ዓመቷ የጀመራት ቆሞ ያለመራመድ ችግር እስካሁን የትም ሃኪም ቤት ቢወስዱዋት መፍትሄ ማግኘት አለመቻሉንም አብራርተዋል።

«ይህ በአከባቢያችን ወርቅ የሚያወጣው ሜድሮክ ለገደንቢ ኩባንያ ይሄው ልጆቻችንን ሰው እንስሳውን እየጎዳብን ነው፡፡ ከዚህ በፊት ሲደርስ የነበረውን ጉዳት ተከትሎ ኮሚቴ ተቋቁሞ የተጎዱ እንዲታከሙ፤ የካሣ ክፍያም እንዲከፈል ተብሎ ነበር፡፡ በዚያው መሰረት የተወሰነ ክፍያ ለአካል ጉዳተኞች እንዲከፈል ሆኗል፡፡ ነገር ግን ያ ክፍያም በቂ ነው የሚል እምነት የለም፡፡ ህክምናም ቢሆን ከተገባው ቃል ባሻገር የተፈጸመልን ነገር አላየንም፡፡ በወቅቱ ለእኔ አሁን የተከፈለኝ 1.2 ሚሊየን ነበር፡፡ ያ ክፍያ ደግሞ ለሁሉም እኩል የተዳረሰ አልነበረም፡፡ እስካ 400 ሺህ ብር የተከፈላቸው፤ ምንም ያልተከፈላቸውም ነበሩ፡፡ 25 አካባቢ ለምንሆን ካሣ ተከፍሎ ከ60 በላይ ለሚሆኑ ያም መከፈሉን እርግጠኛ አይደለሁም። ችግሩ አሁንም ድረስ የቀጠለ ሆኗል፡፡ ኬሚካል ያለጥንቃቄ ይደፋል ከብቶችን ይገድላል ሰውንም ይጎዳል፡፡ ይሄው እስከ ትናንት ከብቶች እየሞቱ ነው፡፡»

ዓለም አቀፉ የሰብኣዊ መብት ተቆርቋሪ ተቋም ሂዩማን ራይትስ ዎች ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ፤ በለገደንቢ ወርቅ የሚያወጡ ኩባንያዎች አሁንም ድረስ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል የሚሰጡት ትኩረት አናሳ መሆን ሰዎችን ለጉዳት እየዳረገ ነው ሲል ተችቷል።

ከዚህ ቀደም ጉዳዩ ውዝግብ አስነስቶ የወርቅ ማውጫ ኩባንያው መዘጋቱን ያነሳው ሰሞነኛው የሂዩማን ራይትስ ዎች ዘገባ፤ አሁን ደግሞ የኩባንያዎቹን ዳግም ሥራ መጀመር ተከትሎ የአካባቢው ነዋሪዎች ለመርዛማ የብረት ንጥረነገር እየተዳረጉ መሆኑን አመልክቷል።

Äthiopien Ali Sulayman
አምባሳደር አሊ ሱሌይማን የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የማኅበራዊ ኃላፊነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ምስል Seyoum Hailu/DW

በለገደንቢ ወርቅ ማውጫ የተሰማሩቱ ሚድሮክ ኢትዮጵያ (Midroc Investment Group) እና የስዊዝ ኩባንያው አርጎር ሂረስ (Argor-Heraeus) ከዚህ በፊት በወርቅ ማውጫው ላይ ሲቀርብ የነበረውን  የአካባቢ ብክለት ቅሬታን ችላ ብለው ቀጥለዋል ሲልም ድርጅቱ ወቅሷል።

ሂዩማን ራይትስ ዎች ሥራውን ለመቀጠል ከመንግሥት ፈቃድ ያገኘው ሚድሮክ ያደረገው የአካባቢ ጥበቃ ማሻሻያም እምብዛም ጠንካራ ሆኖ አልታየምም ነው ያለው።

የኢትዮጵያ መንግሥት የለገደንቢ የወርቅ ማውጣት ሥራ እንዲቆም ከአምስት ዓመታት በፊት ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያመጣ ነው በሚል እንዲዘጋ ወስኖ የወርቅ ማውጣት ሥራውን ለሦስት ዓመታት ገደማ ገትቶ ነበር። ይሁንና ከሁለት ዓመታት ወዲህ የማዕድን አውጪዎቹ ወደ ሥራ የተመለሱት ያለ አመርቂ እርምጃ ነው ይላል ሂዩማን ራይትስ ዎች።

በጉጂ ዞን ሻኪሶ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው ለገደንቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ ነጌሳ ቱካና ለዶቼ ቬለ በሰጡት አስተያየትም ይህንኑ አረጋግጠዋል። «ኩባንያው ወደ ሥራ የተመለሰው መንግሥት ይስተካከሉ ያላቸው የቆሻሻ አወጋገዶች ላይ እንኳ ምንም አይነት እርምጃ ሳይወሰድ በነበረበት እና በተለመደው አኳኋን ነው፡፡ ፋብሪካው የሚለቀው ኬሚካል ከምንጮች ጋር ተቀላቅሎ አሁንም ድረስ ሕጻናቱም ከብቶችም እየተጎዱ ነው።»

በማዕድን ማውጫው ቅሬታ የቀረበበት ሚድሮክ ኢትዮጵያ በበኩሉ ወቀሳውን አይቀበልም። ኩባንያው በተለይም ዳግም ሥራውን ከጀመረ ወዲህ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ሥራው ላይ መሰማራቱን ይገልጻል። በወርቅ ማውጫው በስፋት የተሰማራው ሚድሮክ ኩባንያ በበኩሉ በማዕድን መውጫው ላይ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረኩ፤ ማኅበራዊ ኃላፊነቴንም እየተወጣሁ እገኛለሁ ይላል።  ሂዩማን ራይትስ ዎች ባቀረበው ምክረ ሃሳብ ግን መንግሥት በማዕድን አወጣጥ ስርዓቱ ጣልቃ ገብቶ፤ ኩባንያዎቹም ለደረሰው የጤና እክል ካሣ እንዲከፍሉ ብሎም ብክለቱን እንዲያስወግዱ ይገባል ብሏል። የማዕድን አወጣጥ ስርዓቱም በዓለም አቀፍ የአከባቢ እና ጤና ጥበቃ ብሎ በግልጽ አሰራር እንዲመራ መክሯል።

ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ