በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ውጤት
ሰኞ፣ ነሐሴ 22 2015ቡዳፔስት ሃንጋሪ ከተማ ውስጥ ላለፉት ዘጠኝ ቀናት ስታስተናግድ የነበረው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ትናንት ምሽት ተጠናቋል። ትናንት ምሽት በመዝጊያው ዕለት በተከናወኑ ሁለት የፍጻሜ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን ድል አልቀናቸውም ። ምሽት 3 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ላይ አስቀድሞ በተከናወነ የ5 ሺ ሜትር የወንዶች የሩጫ ውድድር የተሳተፉት ዮሚፍ ቀጄልቻ ፣ ሀጎስ ገብረ ሕይወት እና በሪሁ አረጋዊ በቅደም ተከተል 5ኛ 6ኛ እና 8ኛ በመሆን አጠናቀዋል።
ቀጥሎ በተከናወነው የሴቶች የ3 ሺ ሜትር መሰናክል የሩጫ ውድድር ተሳታፊ የነበሩት ሲምቦ ዓለማየሁ፣ ዘርፌ ወንድማገኝ እና ሎሚ ሙለታ በተመሳሳይ በሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ መግባት ሳይችሉ ቀርተዋል።
በቡዳፔስት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሁለቱም ጾታ በመካከለኛ እና ረዥም ርቀቶች የተሳተፈችው ኢትዮጵያ ከዓለም 6ኛ ከአፍሪቃ ደግሞ 2ኛ ሆና አጠናቃለች ። በ10 ሺህ ሜትር የሴቶች የሩጫ ፉክክር ጉዳፍ ጸጋይ እንዲሁም በማራቶን አማኔ በሪሶ ለኢትዮጵያ ወርቅ ያስገኙ አትሌቶች ናቸው ።
ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት ተሰጥቶት የነበረው የ3ሺ ሜትር መሰናክል ራጫ ለሜቻ ግርማ እንደተለመደው የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ሆኗል። ሞሮኳዊው ኤልባላዲ ለተከታታይ አምስተኛ ጊዜ ለሜቻን በማሸነፍ ወርቁን ወደ ሀገሩ ወስዷል። ኢትዮጵያ በለተሰንበት ግደይ፣ ጎቶይቶም ገብረሥላሴ እና ድርቤ ወልተጂ ተጨማሪ የብር ሜዳሊያዎችን ስታገኝ ፤ በእጅጋየሁ ታዬ ፣ ሰለሞን ባረጋ እና ልዑል ገብረሥላሴ ሦስት የነሐስ ሜዳሊያዎችን አሰባስባ በድምሩ 9 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ነው ከዓለም በስድስተኛነት ያጠናቀቀችው። ዉጤቱ ካለፈው ዓመት በአሜሪካ በኦሬገኑ ከተገኘው እጅጉን ያነሰ ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል።
ቡዳፔስት ከረዥም ጊዜ በኋላ ኢትዮጵያ በወንዶች አንድም ወርቅ ያላገኘችበት ውድድር ሆኗል። የፓሪስ ኦሎምፒክ ሊካሄድ ከአንድ ዓመት በታች መቅረቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ለረዥም ዓመታት ትታወቅባቸው ወደ ነበሩ የመካከለኛው እና ረዥም የውድድር መስኮች አሸናፊነት ለመመለስ ከወዲሁ ከፍተኛ ዝግጅት ማድረግ እንዳለባት ያመላከተም ሆኗል።
ታምራት ዲንሳ
ማንተጋፍቶት ስለሺ