1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶማሌ ክልል ሼቤሌ ዞን የጎርፍ መጥለቅለቅ ብርቱ ጉዳት

ማክሰኞ፣ ኅዳር 18 2016

በሶማሌ ክልል በደረሰው የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ 28 ሰዎች መሞታቸውን፤ በእንስሳት ፣ በእርሻ እና መሰረተ ልማቶች ላይም ጉዳት መድረሱ ተገለጸ ። በጎርፍ እና የወንዝ ሙላት ሳቢያ ብርቱ ጉዳት ከገጠማቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው የሼቤሌ ዞን ከሃምሳ ሰባት ሺህ በላይ አባወራዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የዞኑ አስተዳደር ለዶይቼ ቬለ ዐስታውቋል ።

https://p.dw.com/p/4ZXPa
Überschwemmungen in der äthiopischen Region Somali
ምስል Mesay Teklu/DW

በሶማሌ ክልል የደረሰው የጎርፍ አደጋ በከፊል

በሶማሌ ክልል በደረሰው የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ 28 ሰዎች መሞታቸውን፤ በእንስሳት ፣ በእርሻ እና መሰረተ ልማቶች  ላይም ጉዳት መድረሱ ተገለጸ ። በጎርፍ እና የወንዝ ሙላት ሳቢያ ብርቱ ጉዳት ከገጠማቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው የሼቤሌ ዞን ከሃምሳ ሰባት ሺህ በላይ አባወራዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የዞኑ አስተዳደር ለዶይቼ ቬለ አስታውቋል ። በውኃ ተከበው ለሚገኙ አካባቢዎች ምግብ እና መድኃኒት እየቀረበ መሆኑንም ዞኑ ገልጧል ። የድሬዳዋ ወኪላችን መሳይ ተክሉ የጎርፍ ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች መካከል የዞኑ የፌርፌር እና ምስራቅ ኢሚ ወረዳዎችን በአካል ተገኝቶ ተመልክቷል ። በላከልን ዘገባም፦ ነዋሪዎች ጉዳቱን በመግለፅ ተጨማሪ የምግብ እና የመድኃኒት አቅርቦት እንዲኖር ጠይቀዋል ። አብረን እንከታተል። 

የዋቢ ሸበሌ ወንዝ ሙላት

በክልሉ በዋቢ ሸበሌ ወንዝ ሙላት ከተጥለቀለቁ አካባቢዎች አንዱ በሆነው የሼቤሌ ዞን ፌርፌር ወረዳ ቦርኮር ቀበሌ ከሦስት መቶ በላይ ቤቶች ጎርፍ መግባቱን የሚናገሩት የቀዬው ነዋሪ አቶ አብዱልከሪም አህመድ ነዋሪው እየገጠመው ነው ያሏቸውን የመድኃኒት እና ሌሎች ችግሮች ለዶይቼ ቬለ ገልፀዋል ። የተንጣለለውን ውኃ ተገን አድርጎ ወደ መንደሩ ላይ ይመጣል ያሉት አዞ ሌላው ስጋት እንደሆነም ጠቅሰዋል። 

አቶ መሀሙድ አብዱዋሀድ የተባሉ የምስራቅ ኢሚ ወረዳ ነዋሪ ሰሞኑን በአካባቢያቸውበጎርፍ እና የወንዝ ሙላት ሳቢያ እርሻ መበላሸቱን እና በሥራ ላይ የነበሩ የውኃ መምጠጫዎችን መውሰዱን ገልፀው መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

ለተጎጂዎች ርዳታ በሄሊኮፕተር ተደራሽ ለማድረግ ጥረት መኖሩ ተገልጿል
ለተጎጂዎች ርዳታ በሄሊኮፕተር ተደራሽ ለማድረግ ጥረት መኖሩ ተገልጿልምስል Mesay Teklu/DW

«እኔ የኢሚ ነዋሪዎች ሽማግሌ ነኝ ፤ ስለጎርፉ ችግር ለመናገር የዘነበው ዝናብ ያመጣው ጎርፍ እና የወንዙ ሙላት አንድ ላይ ተገናኝቶ ብዙ ችግር ነው ያደረሰብን ። ብዙ ምርት አበላሽቷል የውኃ ፓምፖችንም ወስዷል። በመሆኑም መንግስት እና ሌሎች አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉልን እንፈልጋለን።»

የሼቤሌ ዞን አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ አደን አህመድ አብዛኛው አካባቢ በውኃ በመከበቡ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረስ ችግር እንደነበር ጠቅሰው አሁን በሄሊኮፕተር ተደራሽ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል። ዋንኛው ትኩረት ሕይወት የማትረፍ እና አስፈላጊ ድጋፍ የማድረስ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ስለ ሶማሌ ክልል የጎርፍ መጥለቅለቁ ከመሳይ ጋ የተደረገው ሙሉ የቀጥታ መስመር ቃለ መጠይቅ

የጎርፍ መጥለቅለቁ የጉዳት መጠን

ዞኑ ካሉት ዐሥር ወረዳዎች አብዛኞቹን ያጥለቀለቀው ውኃ ከአምሳ ሰባት ሺህ በላይ አባወራዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን የተናገሩት አቶ አደን የተለያዩ መሰረተ ልማቶች እና እርሻ መበላሸቱን አስረድተዋል።

በቅርቡ በአካባቢው ሲጥል በነበረው ዝናብ የተከሰተው ጎርፍ እና በዋቢ ሸበሌ ወንዝ ሙላት ሳቢያ በወንዙ ዳርቻ ባሉ አብዛኞቹ አካባቢዎች የተከሰተው የውኃ መጥለቅለቅ ዛሬም ድረስ ጠፈፍ አለማለቱን ተመልክተናል።

ከሰማንያ ዓመት ወዲህ ያልታየ በሚል የአካባቢው ነዋሪዎች የሚገልፁት ይህ ክስተት ያስከተለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑንም እንዲሁ።

የጎርፍ እና ውኃ መጥለቅለቅ በሶማሌ ክልል

በሶማሌ ክልል እንዲሁም ክልሉን አቋርጦ የሚፈሰው የዋቢ ሸበሌ ወንዝ መነሻ በሆኑ ከፍተኛ አካባቢዎች በቅርቡ ከወቅት ውጭ የጣለው ዝናብ አሁን ለተከሰተው ችግር መንስዔ መሆኑ ተገልጧል ።
በተለያዩ ዞኖች በደረሰ የጎርፍ እና የውኃ መጥለቅለቅተከትሎ በተለይ በደራሽ ጎርፍ ሳቢያ 28 ሰዎች መሞታቸውን ፣ በእንስሳት ፣ በእርሻ እና በመሰረተ ልማት ላይ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት መድረሱን የሶማሌ ክልል አደጋ ስጋት አመራር ቢሮ ዐስታውቋል ።

መጥለቅለቁ ከሰማንያ ዓመት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ ተብሏል
የጎርፍ አደጋው በአካባቢው ከሰማንያ ዓመት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ ተብሏልምስል Mesay Teklu/DW

ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች ኅብረተሰብ የሚያስፈልገውን የምግብ እና ሌሎች ድጋፎች በክልሉ እና በፌደራል መንግስት እንዲሁም በሌሎች አካላት እየተከናወነ እንደሚገኝ ጽ/ቤቱ ዐስታውቋል።

ጎርፉ በሼቤሌ ዞን በሺህዎች አፈናቅሏል
ጎርፉ በሼቤሌ ዞን ብቻ ከሃምሳ ሰባት ሺህ በላይ አባወራዎች ላይ ጉዳት አድርሷልምስል Mesay Teklu/DW

በተለይ በአብዛኞቹ አካባቢዎች መንገድ በመበላሸቱ ሳቢያ የድጋፍ አቅርቦቱንም ሆነ በውኃው ተከበው የሚገኙ አካባቢዎችን የነፍስ አድን ሥራ በጀልባ እና ሄሊኮፕተር በታገዘ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል ።

መሳይ ተክሉ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ