1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

አዲስ ነገር የታየበት ቅድመ ምርጫ በአሜሪካ

ረቡዕ፣ የካቲት 27 2016

በአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደን እና የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅድመ ምርጫው አሸንፈው ለዋናው ምርጫ ተመልሰው እንደሚገናኙ ይጠበቃል። ትናንት ማክሰኞ በተካኼደው፣«የሱፐር ቱይስዴይ» ቅድመ ምርጫ፣ እስካሁን በታወቀው ውጤት ሁለቱም የሚያስፈልጋቸውን የተወካዮች ድምጽ ማግኘታቸው ታውቋል።

https://p.dw.com/p/4dEZg
ሱፐር ቱስደይ
ለድጋሚው የምርጫ ፉክክር እንደሚቀርቡ የሚጠበቁት ዶናልድ ትራምፕ ምስል Evan Vucci/AP Photo/picture alliance

«ሱፐር ቱይስዴይ»

 

«ሱፐር ቱይስዴይ»

በአሜሪካ የምርጫ ስርዓት ሁለት አበይት ሂደቶች አሉት፤ ቅድመ ምርጫና ዋናው ምርጫ። በቅድመ ምርጫው ሂደት ትናንት ካሊፎርኒያና ቴክሳስን ጨምሮ 15 ግዛቶች የተሳተፉበት ቅድመ ምርጫ ተከናውኗል። በአሜሪካ በሚካሄዱ ምርጫዎች በአስፈጻሚነት የሚሳተፉት ፕሮፌሰር ፀሐይ ዓለማየሁ፣ስለ«ሱፐር ቱይስደይ» ምንነትን ሲያስረዱ፤ «ይህ «ሱፐር ቱይስዴይ» የሚለው አካሄድ የመጣው በዚህ በደቡቡ ያሉ እኛ ግዛት ጆርጂያ ያሉ፣ ሌሎችም በደቡባዊ ዩናይትድስቴትስ ያሉ ግዛቶች፣ እኛ ዐሳባችን፣ አስተያየታችንና ድምፃችንን በደንብ እየተሰማ አይደለም። አንደኛ የመጀመሪያ ተወዳዳሪ ስቴቶች ወደ ሰሜን ያሉ ስቴቶች በመሆናቸው፣ ሁለተኛ ተበትነን የራሳችን ቀን በማድረጋችን፣ በባህላችንም በፖለቲካ ዕይታችንም ተመሳሳይ ሆነን ሳለ፣ በቂ እውቅና አናገኝም ብለው ስላሰቡ፣ በአንድ ቀን ሰባት፣ስምንት፣ ዘጠኝ አስር የተለያዩ ስቴቶች ድምጽ ብንሰጥ ይመቸናል ብለው የዛሬ 20 ዓመት ገደማ ምልባት ከዛም በፊት ሊሆን ይችላል፣ የጀመሩት አካሄድ ነው።» ይላሉ።

የዘንድሮውን ምርጫ ልዩ የሚያደርገው

ከአሜሪካ ኢትዮጵያ የሕዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ(ኤፓክ) ያነጋገርናቸው አቶ ነብዩ አስፋው፣ የዘንድሮውን «ሱፐር ቱይስዴይ» ልዩ ስለሚያደርጉ ጉዳዮች ሲናገሩ፤ «የዲሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩ ተቀማጩ ፕሬዝዳንት ባይደን ስለሆነ፣ ይህን ያህል ብዙ እንቅስቃሴ የለም። እሱን የሚገዳደረው ሰው ስለሌለ ፣በሪፐብሊካን በኩል ደግሞ፣ የዘንድሮን ልዩ የሚያደርገው፣ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራሞፕ በጆ ባይደን ከሥልጣናቸው ተነስተው ነበር። አሁን ደግሞ ተመልሰው ወደ ሥልጣን ለመምጣት እየተወዳደሩ ነው፤ እንግዲህ በአሜሪካ ብዙም የተለመደ አይደለም።» በማለት እንዲህ ያለው አጋጣሚ  በአሜሪካ ታሪክ አዲስ እንደሆነና፤ ምናልባትም የዛሬ 200 ዓመት አንዴ ተከስቶ እንደነበር ነው የተናገሩት።

ሱፐር ቱስደይ
በቅድመ ምርጫው በርካታ አሜሪካውያን ተሳትፈዋል።ምስል Robert F. Bukaty/AP Photo/picture alliance

ባይደንና ትራምፕ እንደገና

በትናንቱ «ሱፐር ቱይስደይ» እንደተገመተው ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደንና የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቂ የተወካዮች ድምጽ አግኝተው በማሸነፍ፣ በድጋሚ ለዋናው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ እንደገና እንደሚገናኙ ይጠበቃል። የሕግ ባለሙያው ዶክተር ፍፁም አቻምየለህ ግምትም ይኸው ነው። በርካታ የአሜሪካ መራጮች፣ ባይደንና ትራምፕ ተመልሰው ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ መቅረባቸው አይዋጥላቸውም። ከዚህ አኳያ የሀገሪቱ የፖለቲካ መድረክ አዲስ ሰው ይዞ መምጣት ያልቻለበት መሠረታዊ ምክንያት መነጋገሪያ ሆኗል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በምርጫው ክፉኛ የተሸነፉት የትራምፕ ተፎካካሪ ኒኪ ሄሊ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዘመቻቸውን ማቋረጣቸውን ከአንድ ሰዓት በፊት አስታውቀዋል። የ52 ዓመቷ ሄሊ ይህንኑ ውሳኔያቸው ባሰወቁበት መግለጫቸው ምንም የሚጸጽታቸው ነገር እንደሌለ ተናግረዋል። የሄሊ ስንብት ትራምፕ በመጪው ህዳር በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከርሳቸው ጋር በሚወዳደሩት በባይደን ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ያደርጋቸዋል።

ታሪኩ ኃይሉ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ