መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ራሳቸውን ለሱዳን መሪነት እያዘጋጁ ወይስ...?
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 29 2016ለርዋንዳ የዘር ፍጅት በኪጋሊ የተመሠረተው መታሰቢያ የጎበኙትን በሐዘን ማቅ የሚያለብስ ነው። መታሰቢያው ከ250,000 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ሰለባዎች የመጨረሻ ማረፊያ ነው። መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ባለፈው ዓርብ መታሰቢያውን ከጎበኙ በኋላ “የርዋንዳ የጥልቅ ቁስል እና የብርቱ መከራ ዘመን” ምስክር ሲሉ ገልጸውታል።
ዳጋሎ ርዋንዳውያን ችግሮቻቸውን ፊት ለፊት ተጋፍጠው ጋካቻ በተባለ የሽግግር ፍትኅ ሥርዓት “ሥር-ነቀል መፍትሔዎች” ተግባራዊ ማድረጋቸውን ያደንቃሉ። ርዋንዳውያን የተከተሉት መንገድ ታሪካቸውን “ከመከፋፈል ወደ አንድነት፣ ከጥላቻ ወደ ፍቅር፣ ከጦርነት ወደ ሠላም እና ዘላቂ ልማት” እንደቀየረ የገለጹት ዳጋሎ “እንደ ሱዳናዊ ከርዋንዳ መማር አለብን” የሚል ዕምነት አላቸው።
ሱዳን የገጠማት ጦርነት “የመጨረሻው ሊሆን ይገባል” ያሉት መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ “ለራሳችን ፍትኃዊ እና ዘላቂ ሠላም ለመጪው ትውልድ ብልጽግና ለመፍጠር መስራት አለብን” ባይ ናቸው። የዳጋሎ አማላይ ሐሳብ በሱዳን በተለይ በዳርፉር እርሳቸው የሚመሩት ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የሚወነጀልበት “የዘር ፍጅት” ሲታሰብ መገበዝ ይመስላል።
የማሳሊት ሰዎች ሰቆቃ
ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት አረብ ያልሆኑ የዳርፉር ነዋሪዎች ተገፍተናል በሚል ቅሬታ ነፍጥ ሲያነሱ የቀድሞው ፕሬዝደንት ዑመር አልበሽር መንግሥት በአብዛኛው አረብ የሆኑ ታጣቂዎች አዘመተባቸው። ጃንጃዊድ ተብለው የሚጠሩት ታጣቂዎች መጠነ-ሰፊ ግፍ በመፈጸም ይወነጀላሉ። አብዛኞቹ የጃንጃዊድ ታጣቂዎች ላለፉት ዘጠኝ ወራት ከሱዳን ጦር ውጊያ የገጠመውን የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ተቀላቅለዋል።
ባለፈው ኅዳር ወር በመቶዎች የሚቆጠሩ የማሳሊት ጎሳ አባላት በምዕራብ ዳርፉር ግዛት አርዳማታ ከተማ በፈጥኖ ደራሽ ኃይል እና አጋር ሚሊሺያዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል። አብዛኞቹ የጥቃቱ ሰለባዎች ወንዶች በተለይም ወጣቶች እና አዳጊዎች ናቸው።
አዋቴፍ አዳም ያሳድጉት የነበረ የእህታቸው የ12 ዓመት ልጅ በፈጥኖ ደራሽ ኃይል እና አጋር የአረብ ሚሊሺያዎች እንደተገደለ ይናገራሉ። “ጭንቅላቱ ላይ መቱት፤ በእንጨት በትር ሲደበድቡት ነበር” የሚሉት አዋቴፍ “እንደ አባት ያሳደገው ባለቤቴ ሊያድነው ቢሞክርም አልቻለም። እየጎተቱ ወስደው በዱላ እየደበደቡ እንዲድህ አዘዙት። ደሙ ፈሶ ሲሞት ጥለንው ሔድን” ሲሉ የደረሰበትን አስረድተዋል።
በዳርፉር ሱዳን ያገረሸው የጅምላ ግድያ እና የሴቶች ጾታዊ ጥቃት
አሜሪካ ሉቴናንት ጄኔራል አብዱል ፋታኅ አል-ቡርኻን የሚመሩት የሱዳን ብሔራዊ ጦር እና በሉቴናንት ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሚታዘዘው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የጦር ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሳለች። የዳጋሎ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል እና አጋር ሚሊሺያዎች በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እና የዘር ፍጅት መፈጸማቸውን አሜሪካ እንደደረሰችበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አንቶኒ ብሊንከን ገልጸዋል።
ያሳደጉት የእህታቸው ልጅ የተገደለባቸው አዋቴፍ አዳምን ጨምሮ በምሥራቃዊ ቻድ ከሱዳን ድንበር አቅራቢያ አድሬ በተባለ ቦታ ብቻ ጦርነቱን የሸሹ 500 ሺሕ ገደማ ስደተኞች ይገኛሉ። በሱዳን ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ሰባት ሚሊዮን ዜጎች በዚያው በሀገራቸው ተፈናቃይ ሆነዋል። ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል። ከ12 ሺሕ በላይ ሰዎች ገድለዋል።
የጦርነቱ ዋንኛ ባለቤቶች ማለትም የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በድርድር ውጊያውን ለማቆም ፈቃደኛ ሆነው አልተገኙም። ጦርነቱ በተፋፋመባቸው ወራት ተደብቀው የቆዩት የፈጥኖ ደራሹ ኃይል አዛዥ ሉቴናንት ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ባለፈው ሣንምንት የሀገራቸውን ሲቪል ፖለቲከኞች እና የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችን ልብ ለማሸነፍ ወዲህ ወዲያ ሲሉ ሰንብተዋል።
ሲሪል ራማፖሳ በመኖሪያ ቤታቸው “የሱዳን ፕሬዝደንት መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎን ተቀብለው አነጋገሩ” የሚል ዓረፍተ ነገር ባለፈው ሐሙስ በደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ማኅበራዊ መገናኛዎች ብቅ ሲል ቁጣ ተቀስቅሶ ነበር። የፕሬዝደንቱ ጽህፈት ቤት በቀድሞው ትዊተር የአሁኑ ኤክስ የተሰራጨውን መረጃ አጥፍቶ የመሐመድ ሐምዳን ዳጋሎን ማዕረግ “የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ መሪ” በሚል ቀየረ።
ሱዳን ውስጥ የተፈጸሙ የጦር ወንጀሎች በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት መታየት መጀመራቸው
ራማፖሳን ለትችት የዳረጋቸው ግን በጽህፈት ቤታቸው ዳጋሎ “የሱዳን ፕሬዝደንት” ተብለው መጠራታቸው ብቻ አልነበረም። በጋዛ ጦርነት ምክንያት እስራኤልን ከዓለም አቀፉ የጦር ፍርድ ቤት የከሰሰ መንግሥት የሚመሩት ራማፖሳ “በዳርፉር የዘር ፍጅት ፈጽሟል” ተብሎ ከሚወነጀለው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪ እጅ ለእጅ ተጨባብጠው መታየታቸው አልተወደደላቸውም።
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዥ ወደ ደቡብ አፍሪካ ከማቅናታቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ከኬንያ ፕሬዝደንት ኦፊሴላዊ መኖሪያ ቤት ሲደርሱ እንደ ሀገር መሪ ቀይ ምንጣፍ ተዘርግቶ ዊሊያም ሩቶ “ጥሩው ወንድሜ ወደ ናይሮቢ እንኳን ደሕና መጡ” ብለው ተቀብለዋቸዋል።
ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ከውይይቱ በኋላ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል እና መሪው መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ “የሱዳንን ግጭት በውይይት ለማቆም ያላቸውን ቁርጠኝነት ኬንያ ታደንቃለች” ብለዋል። የምሥራቅ አፍሪካ በይነ-መንግሥታት (ኢጋድ) እያካሔደ የሚገኘው ሽምግልና ለሱዳን ዘላቂ ሠላም የሚፈጥር ፖለቲካዊ እልባት ማምጣት እንዳለበትም የኬንያው ፕሬዝደንት ገልጸዋል።
የዳጋሎ የኬንያ ጉብኝት ግን እንደ ደቡብ አፍሪካው ሁሉ ውዝግብ አላጣውም። ኬንያ ለዳጋሎ ባደረገችው አቀባበል የተቆጣችው ሱዳን አምባሳደሯን ወደ ኻርቱም ጠርታለች።
ማሕደረ ዜና፣ የሱዳን ጦርነት፣ የተቃራኒ መሪዎቿ- ተቃራኒ መልዕክት
የሱዳን ጦርነት እንደተቀሰቀሰ ሁለቱን ኃይሎች የማደራደር ኃላፊነቱን በኢጋድ በኩል ቀደም ብለው ከወሰዱ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት አንዷ የሆነችው ኬንያ ከዳጋሎ ያላትን ግንኙነት እንዲቀጥል ማድረጓ በኻርቱም መንግሥት እምብዛም አልተወደደላትም።
ዳጋሎ ባለፈው ሣምንት በዩጋንዳ ከፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ፣ በኢትዮጵያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ በጅቡቲ ከፕሬዝደንት ኢስማኤል ዑመር ጉሌሕ በመጨረሻም በርዋንዳ ከፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ ተገናኝተዋል። በሁሉም ወገን በተሰጡ መግለጫዎች መሠረት አብዛኛው ውይይታቸው ጦርነቱን ለማቆም በሚደረገው ጥረት ላይ ያተኮረ ነበር።
ጉዳዩን በቅርብ ለሚከታተሉ ባለሙያዎች ግን የዳጋሎ ጉዞ ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ጋር የተገናኘ ስትራቴጂ ነው። የሱዳን ጉዳዮች ተመራማሪው አሌክስ ደዋል እንዲያውም ዳጋሎ እያንሰራሩ ነው ሲሉ ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።
በሶርቦን ዩኒቨርሲቲ የሱዳን ጉዳዮች ተመራማሪው ክሌመንት ዲዬ ዳጋሎ በሔዱበት ሁሉ እንደ ሀገር መሪ “እንኳን ደህና መጡ” የሚል አቀባበል እንደገጠማቸው ያምናሉ። ከሁሉም የሚበልጠው ግን ዲዬ ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብደላ ሐምዶክ በአዲስ አበባ የጀመሩት ግንኙነት ነው።
ሐምዶክ ባለፈው ሣምንት የሲቪል ፖለቲከኞች ያቋቋሙትን ጥምረት ወክለው ከዳጋሎ ጋር “የአዲስ አበባ አዋጅ” የተባለ ሥምምነት ፈርመዋል። ይኸ አዋጅ ወደፊት ለሚደረጉ ድርድሮች መሠረት ሆኖ እንዲያገለግል የታቀደ ነው።
ዳጋሎ ሥምምነቱን ከፈረሙ በኋላ “ሰነዱን ከአንድ ቀን በፊት አንብቦ ዛሬ ለመፈረም የሚቻል አልነበረም። ነገር ግን አድርጌዋለሁ። ምክንያቱም አጀንዳ የለኝም። ሰነዱ ጦርነቱን ማቆምን እንደሚያካትት ተመልክቺያለሁ። ይኸ የእኔም ፍላጎት ነው። ጦሩ ተመሳሳይ ሰነድ ይዞ ቢመጣ አሁኑኑ እፈርመዋለሁ” ሲሉ ተኩስ ለማቆም ፈቃደኛ ለመሆናቸው ጥቆማ ሰጥተዋል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብደላ ሐምዶክ የሲቪል ዴሞክራሲያዊ ኃይሎችን ወክለው የፈረሙት የአዲስ አበባ አዋጅ የሱዳን ጦር ሠራዊት እና ዳጋሎ የሚመሩት ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በቀጥታ ድርድር “በአፋጣኝ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ግጭት” እንዲያቆሙ ለማድረግ ያቀደ ነው። ሐምዶክ “አንድ ጦር ብቻ እንደሚኖር በዐዋጁ ተስማምተናል። እነዚህ በርካታ ወታደራዊ አደረጃጀቶች እያሉ ሱዳን ሠላማዊ ሀገር ሆና የምትዘልቅበት ምንም አይነት ዕድል የለም” ሲሉ ተናግረዋል።
ዳጋሎ እንዳሉት የአዲስ አበባው አዋጅ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ወደ መኖሪያ ቤቶቻቸው እንዲመለሱ የሚያደርግ ቃል ኪዳን ጭምር ያካተተ ነው። ጦርነቱን ለማቆም በሚደረጉ የሠላም ንግግሮች ሲቪል ፖለቲከኞች ሊካተቱ እንደሚገባ በሰነዱ ሰፍሯል።
በአሜሪካ በሰብዓዊነት ላይ ወንጀል ፈጽሟል ተብሎ የሚወነጀለው እና ባለፉት ሣምንታት በሱዳን አውደውጊያዎች ዕድል የቀናው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ምን ያክል ሥምምነቱን ያከብራል የሚለው ጉዳይ ግን አሁንም መልስ አላገኘም። ባለፈው ማክሰኞ ዳጋሎ ሥምምነቱን ከፈረሙ በኋላ ግን ቢያንስ ይቅርታ ጠይቀው የሱዳናውንያን ልብ ለማሸነፍ ሞክረዋል።
ዳጋሎ በአረብኛ ታቅደም ተብሎ የሚጠራውን የሲቪል ፖለቲከኞች ጥምረት በመጠጋት “ተቀባይነት ለማግኘት የሚረዳቸውን አንድ እጅግ ጠቃሚ እርምጃ” እንደወሰዱ በለንደን ኪንግስ ኮሌጅ የሱዳን ጉዳዮች ተመታማሪው አንድሪያስ ክሬይግ ያምናሉ። ይኸ ተቀባይነት የጦር አበጋዙ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም ከምዕራባውያኑ አጥብቀው የሚፈልጉት ነው።
ሱዳናዊቷ ኹሉድ ኼይር የአዲስ አበባው ስብሰባ ዳጋሎ የበላይ ሆነው የታዩበት እንደሆነ ገልጸዋል። ዳጋሎም “ዛሬ ላይ ቆመን እጃችንን ለሠላም እየዘረጋን ነው። ሠላምን ከፈለጉ በጸጋ እንቀበላቸዋለን። ከሠላም ውጪ ከኻርቱም እንድንወጣ የሚያደርገን የለም” በማለት ራሳቸውን የሠላም መሲህ አድርገው ለማቅረብ ሞክረዋል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመሩት የሲቪል ፖለቲከኞች ጥምረት የፈረመው ሥምምነት ከሱዳን ማኅበራት እና የለውጥ አቀንቃኞች ድጋፍም፤ ተቃውሞም ገጥሞታል። ፖለቲከኞቹ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የመሠረቱት አጋርነት ያሰጋቸውም አልጠፉም።
“ዕርቅ የለም” አብዱል ፋታኅ አል-ቡርኻን
የሱዳን ጦር አዛዥ አብደል ፋታኅ አል-ቡርኻን ግን ሥምምነቱን ውድቅ አድርገዋል። የዳጋሎን የሠላም ጥሪ ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆኑም። የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤትን በሊቀ-መንበርነት የሚመሩት አል-ቡርኻን ባለፈው ዓርብ ጀበይት በተባለ የጦር ትምህርት ቤት ለወታደሮች ያደረጉት ንግግር ቁጣ የተጫነው ነበር።
“የሲቪል ኃይሎች ዓለም እንደ አሸባሪ ከሚቆጥረው አመጸኛ ሕገ-ወጥ ቡድን ጋር ሥምምነት ተፈራርመዋል” ያሉት አል-ቡርኻን የአዲስ አበባው አዋጅ “ተቀባይነት የለውም” ሲሉ ተደምጠዋል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብደላ ሐምዶክ ሥምምነቱን ከፈረሙ በኋላ ባለፈው ረቡዕ አል-ቡርኻን ከሲቪል ፖለቲከኞች ጥምረት ተገናኝተው እንዲወያዩ ጋብዘዋል። አል-ቡርኻን ሥምምነቱን ውድቅ ቢያደርጉም ከፖለቲከኞቹ ጋር በፖርት ሱዳን ተገናኝተው ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
“መላው ዓለም እነዚህ አማጺ ኃይሎች በምዕራብ ዳርፉር እና በሁሉም የሱዳን ክፍሎች የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ ወንጀሎች መፈጸማቸውን ታዝቧል” ያሉት አል-ቡርኻን ለወታደሮቻቸው ባሰሙት ንግግር “በዚህ ምክንያት ከእነርሱ ጋ ዕርቅ የለንም፤ ከእነርሱ ጋ ሥምምነት የለንም” ሲሉ ተደምጠዋል።
አል-ቡርኻን “ከሀዲ” እና “ፈሪ” እያሉ ከዘረጠጧቸው ዳጋሎ ጋር ለመገናኘት ፈቃደኛ እንዳልሆኑም ተናግረዋል። ጅቡቲ በሊቀ-መንበርነት የምትመራው የምሥራቅ አፍሪካ በይነ-መንግሥታት (ኢጋድ) አል-ቡርኻን እና ዳጋሎ ፊት ለፊት ለመገናኘት መስማማታቸውን አስታውቆ ነበር።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ሰባት አገሮች የሱዳንን ውጊያ ለማቆም የሚያደርጉትን ጥረት የማስተባበሩን ኃላፊነት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው ሰጡ
አል-ቡርኻን ኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኬንያን ጨምሮ ለዳጋሎ ኦፊሴላዊ አቀባበል ያደረጉ የአፍሪካ ሀገራትን አጥብቀው ኮንነዋል። ዳጋሎ “የሱዳንን ሕዝብ እያዋረደ፣ እየገደለ፣ እየዘለፈ ነው” ያሉት አል-ቡርኻን “አንዳንድ ሰዎች እያጨበጨቡለት አብረው ይስቃሉ” ሲሉ ኮንነዋል።
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይልን ለመዋጋት የሚፈልጉ የሀገራቸው ዜጎችን ለማስታጠቅ ቃል ገብተዋል። ጦሩን እንዲቀላቀሉም ጥሪ አቅርበዋል። ሱዳን ወደ “ባርነት እና ቅኝ አገዛዝ” የመውደቅ ሥጋት እንደተጋረጠባ ጭምር አል-ቡርኻን ተናግረዋል። ይኸኛው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን በመደገፍ በምትከሰሰው የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ላይ ያነጣጠረ ይመስላል።
የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት፣ ግብጽ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና አሜሪካ ተደጋጋሚ ጥረቶች ቢያደርጉም ሁለቱ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች እስካሁን በድርድር ጦርነቱን ለማብቃት ፈቃደኛ አልሆኑም። ተንታኞች እንደሚሉት ሁለቱም እናሸንፋለን ብለው ያምናሉ።
እሸቴ በቀለ
ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር