ሒዝቦላሕ መሪው ሐሳን ናስረላሕ መገደላቸውን አረጋገጠ
ቅዳሜ፣ መስከረም 18 2017የሊባኖሱ ሒዝቦላሕ መሪው ሐሳን ናስረላሕ እስራኤል በፈጸመችው የአየር ጥቃት መገደላቸውን አረጋገጠ። ታጣቂ ቡድኑ በእስራኤል ላይ ያወጀውን እና “ቅዱስ” ያለውን ጦርነት እንደሚቀጥል ዝቷል።
የእስራኤል ጦር በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ደቡባዊ ክፍል በፈጸመው ጥቃት ሐሳን ናስረላሕ መገደላቸውን ቀደም ብሎ አስታውቆ ነበር። በኢራን የሚደገፈው ቡድን ዛሬ ባወጣው መግለጫ መሪው መገደላቸውን አረጋግጧል።
በዋና ጸሀፊነት ሒዝቦላሕን ለ30 ዓመታት የመሩት “ሳይድ ሐሳን ናስረላህ ታላላቅ ዘላለማዊ ሰማዕት ጓዶቻቸውን ተቀላቅለዋል” ብሏል። ሐሳን ናስረላሕ የተገደሉት ከሌሎች የሒዝቦላሕ አባላት ጋር ነው።
ሒዝቦላሕን የምታስታጥቀው እና በገንዘብ የምትደግፈው ኢራን የአብዮታዊ ዘብ ከፍተኛ አባል በጥቃቱ መገደላቸውን ገልጻለች።
በአደባባይ የማይታዩት ናስረላሕ በሺዓ እስልምና ተከታይ ደጋፊቻቸው ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው ነበሩ። በሊባኖስ ጦርነት የማወጅም ይሁን ሰላም የማውረድ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደነበራቸው የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳንኤል ሐጋሪ በቴሌብዥን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሐሳን ናስረላሕ “ከእስራኤል ታላላቅ ጠላቶች አንዱ ነበሩ” ብለዋል። ቃል አቀባዩ “መወገዳቸው ዓለምን የበለጠ አስተማማኝ ያደርገዋል” ሲሉ ተደምጠዋል።
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ናስር ቃናኒ ሐሰን ናስረላሕ ቅዱስ ዓላማ “እንደ ፈጣሪ ፈቃድ ኢየሩሳሌምን ነጻ በማውጣት ይፈጸማል” ሲሉ በኤክስ ጽፈዋል።
የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላ አሊ ኻሚኒ ቀደም ብለው ባስተላለፉት መልዕክት የናስረላሕን እጣ ፈንታ ባይገልጹም የእስራኤልን “አርቆ ማየት የተሳነው ደደብ ፖሊሲ” በማለት መንቀፋቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
ሒዝቦላሕ የመካከለኛው ምሥራቅን ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ጉልህ ሚና እንደሚጫወት የገለጹት ኻሚኒ ሁሉም የእስልምና እምነት ተከታዮች ከእስራኤል በሚደረገው ውጊያ እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።
የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሐማስ የናስረላሕን ግድያ “የፈሪ የሽብር ተግባር” በማለት ኮንኗል።
ሒዝቦላሕ በእስራኤል ላይ አነስተኛ ድንበር ተሻጋሪ ጥቃቶች መፈጸም የጀመረው መስከረም 26 ቀን 2016 ከተፈጸመው እና በጋዛ ጦርነት ከቀሰቀሰው የሐማስ ጥቃት በኋላ ነው።
ከጋዛ ፊቷን ወደ ሊባኖስ ያዞረችው እስራኤል በፈጸመቻቸው ጥቃቶች ከ700 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የተባበሩት መንግሥታት በሊባኖስ 118,000 ሰዎች መፈናቀላቸውን አስታውቋል። ባለፈው አንድ ሣምንት ሊባኖስ እና እስራኤል የሚዋሰኑትን ድንበር የሚሻገሩ ጥቃቶች ቁጥር በከፍተኛ መጠን ጨምሯል።