1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትአፍሪቃ

ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና የሚደረገው ዝግጅት

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 1 2015

የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ መሰጠት መጀመሩ አጠቃላይ የሀገሪቱ የትምህርት ስረዓት ገመና አደባባይ የወጣበት ነው ሲሉ በርካቶች አስተያየታቸውን ሲሰጡ ይደመጣሉ ። ሁኔታው በየትምህርት ቤቱ መደናገጥን ፈጥሮም ነበር ።

https://p.dw.com/p/4TWtF
Äthiopien Vorbereitungen Studenten auf Prüfungen
ምስል privat

የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በተለያየ ሁኔታ ውስጥ ለፈተና እየተዘጋጁ ነው

ተማሪ ስምረት አብዩ ትባላለች ። በጅማ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ መሰናዶ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነች ። ትናንት ሐሙስ ቀትር ላይ የሞዴል ፈተና ተፈትና ስትወጣ ነበር በስልክ ያነጋገርኳት። እርሷም ሆነች ጓደኞቿ ከወትሮ በተለየ ሁኔታ ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ዝግጅት እያደረገች መሆኗን ትናገራለች። 
«ያው እንግዲህ ዘንድሮ እንደሚታወቀው የፈተናው ስረዓት ለየት ባለ መልኩ እየተሰጠ ይገኛል። እናም ለዚሁ የሚመጥን ዝግጅት እያደረግን ብዬ በልበ ሙሉነት መናገር እችላለሁ እኔም ሆንኩ ጓደኞቼ ያለንን ጊዜ ሙሉ ለፈተናው ዝግጅት ለማዋል እየጣርን ነው »
ሰላም ጤና ይስጥልን የዝግጅታችን ተከታታዮች ሳምንት ጠብቆ በዚህ ሰዓት የሚደመጠው የከወጣቶች ዓለም ዝግጅታችን እነሆ ጀምሯል። የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ አልያም የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ካለፈው ዓመት ጀምሮ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ መሰጠት ጀምሯል። በ2014 ዓ.ም በተሰጠው ሀገር አቀፍ ፈተና በሁለቱም የትምህርት መስክ ፈተናውን ከወሰዱት 896 ሺህ 520 ተማሪዎች ውስጥ 29 ሺህ 909 የሚሆኑት ተማሪዎች 50% እና በላይ ያስመዘገቡ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስቴር ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡ ይህም በመቶኛ ሲሰላ ያለፉ ተማሪዎች ቁጥር  3,4 በመቶ ይሆናል። ዉጤቱ ይፋ እንደተደረገ በበርካቶች ዘንድ መደናገጥን ከመፍጠሩ በተጨማሪ የሀገሪቱ የትምህርት ጥራት ውድቀት ማሳያ ስለመሆኑም በየመገናኛ  ብዙኃኑ አነጋግሯል። ስምረት እንደምትለው ፈተናው በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ መሰጠቱ መኮራረጅን አስቀርቶ በራስ መተማመኗን ጨምሮላታል።
«እኔ በይበልጥ በቀናነቱ ነው የምወስደው ። ምክንያቱም አንደኛ በየትምህርት ቤቱ የነበረውን የኩረጃ ሁኔታ በመቀነስ ረገድ ትልቅ አስተዋጽዖ አበርክቷል ብዬ አስባለሁ ። በተጨማሪም ደግሞ ለጎበዝ ተማሪዎች በየትምህርት ቤቶች ከነበረባቸው ጫና አንጻር ቀንሶላቸዋል ብዬ አስባለሁ።»
በባህርዳር ከተማ በሚገኘው እሸት አካዳሚ የምትማረው ተማሪ ሃና ሙሉሰውም የስምረትን ሃሳብ ትጋራለች።
«በዩኒቨርሲቲ ውስጥ መፈተናችን ለራሳችንም በራስ መተማመን እንዲያድርብን አድርጓል። ማለት መቀዳዳት ፣ መኮራረጅ እና የተለያዩ ነገሮችን ቀንሶልናል።  » 
የአሶሳ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪው ያሬድ አስቻለው እንደሚለው ደግሞ ከፈተናው ጋር ተያይዘው የሚናፈሱ ወሬዎች ለፈተናው በሚያደርገው ዝግጅት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረበት ነው ። ፈተናው አክብዶ እንዲመለከት እያደረገው ነው።  
«ሁላችንምጋ ከህዝቡ ጋር በተያያዘ ከባድ እንደሆነ ተነግሮናል። ባለፈው ዓመት ከተፈተኑት ልጆች በመጠየቅም ሆነ በሚዲያ ላይ በሚደረጉ ንግግሮች ትንሽ ያጨናንቃል። ነገር ግን ያው እኛ ከባለፈው ዓመት ከተፈተኑት የፈተና ወረቀት በመውሰድ  ከጓደኞቻችን ጋር ሰብሰብ ብለን እየሰራን ነው»

Äthiopien Vorbereitungen Studenten auf Prüfungen
ተማሪ ሃና ሙሉሰው በጥናት ላይ ምስል privat
100,000 Books donation for  damaged schools in Ethiopia
የኢትዮጵያ የትምህርት ሚኒስቴር አርማ ምስል Hanna Demisse/DW

የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ መሰጠት መጀመሩ አጠቃላይ የሀገሪቱ የትምህርት ስረዓት ገመና አደባባይ የወጣበት ነው ሲሉ በርካቶች አስተያየታቸውን ሲሰጡ ይደመጣሉ ። ሁኔታው በየትምህርት ቤቱ መደናገጥን ፈጥሮም ነበር ። ለወትሮ በርካታ ተማሪዎችን ያሳልፉ የነበሩ ትምህርት ቤቶች ጭምር ከፍተኛ ውድቀት ገጥሟቸው እንደነበር ጭምር ሲነገር ቆይቷል። ለመሆኑ ፈተናው በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ መሰጠቱ ትምህርት ቤቶችን ምን ያህል አንቅቷቸው ይሆን ? ለተማሪዎቻቸውስ ምን ያህል ድጋፍ እያደረጉ ይሆን? ተማሪዎቹ ይናገራሉ ። 
« ዘንድሮ ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች ሰፊ የማጠናከሪያ ትምህርት አገልግሎት ተዘጋጅቶልናል።  ከዚህም በተጨማሪ የስነ ልቦና ዝግጅት እንድናደርግ ጥረት አድርገውልናል። የመጽሐፍት እና የቁሳቁስ አቅርቦትም አቅም በፈቀደው መሰረት ጥረት እየተደረገ ነው»
የባህርዳሯን ሃናን ያናገርናት የሞዴል ፈተና እየተፈተነች በነበረበት ወቅት ባገኘችው ፋታ ነበር። ለዋናው ፈተናው ያግዝ ዘንድ የክልሉ ትምህርት ቢሮ የሞዴል ፈተና አዘጋጅቷል። በእርግጥ ለዚህ ዝግጅት ያነጋገርናቸው ተማሪዎች ሁሉም የሞዴል ፈተና እየተፈተኑ መሆናቸውን ነግረውናል ፤ ይህስ ለዋናው ፈተና ምን ያህል ጠቅሟቸው ይሆን  ? 
« የክልሉ ሞዴል ለዋናው ፈተና እንዲኢዘጋጅ አድርገው ነው ጥያቄውን ያወጡት ትንሽም ከበድ ይላል ግን ለዚያናው ፈተና እንድንዘጋጅ አድርገው ነው ጥያቄውን ያወጡት እና ጥሩ ነው »

Äthiopien Vorbereitungen Studenten auf Prüfungen
ተማሪ ሃና ሙሉሰው በጥናት ላይ ፤ ባህርዳር ምስል Privat

የአሶሳው ያሬድ ግን የትምህርት ቤቶች የአቅም ውስንነት በፈተና የዝግጅት ሂደት የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ በአግባቡ እንዳይወጡ እንቅፋት እንደፈጠረባቸው ይረዳል። 
«በአካባቢያችን ትንሽ የቤተ መጽሐፍት የተሟሉ ስላልሆኑ ትንሹ እሱ ይከብዳል። እና ደግሞ የፈተናው ነገር ትንሽ ያሳስባል። እሱ በአብዛኛው ሰው ጋ የተለያየ ነገር ስለሚነሳ እና ከባድ ነው ስለሚሉን እነሱ እነሱ ትንሽ ያጨናንቃሉ።»
በተለያየ የትምህርት አካባቢ አድገው እና ተምረው በተመሳሳይ ሁኔታ  ፈተናው ላይ ሲቀመጡ ተወዳዳሪ መሆን እንደምን ይቻላቸው ይሆን  ? ጥያቄ ነው። የሆነ ሆኖ ተማሪዎቹ ከፈተናው ባሻገር የየራሳቸው ህልም እንዳላቸው ይናገራሉ ። 
ተማሪዎቹ ህልማቸውን ለመኖር ተግተው ማጥናት ይኖርባቸዋል። በትምህርት ቤት ፣ በወላጆች እና በአጠቃላይ በማህበረሰቡ የተናጥል እና የተቀናጀ ድጋፍም እንዲሁ ያሻቸዋል። የሀገሪቱ የትምህርት ስረዓትም የፈተና ደህንነትን ለማስጠበቅ የሚያደርገው ጥረት አንድ ነገር ሆኖ የሀገሪቱን የትምህርት ጥራት ከመሰረቱ የናዱ ጉዳዮችን ለይቶ መፍትሄ ካላበጀ ዉሃ መውቀጥ እንዳይሆንበት ያሰጋል። መኮራረጅ ሌብነት ፤ ሌብነት ደግሞ አስጸያፊ ተግባር መሆኑን ልጆች ገና ከህጻንነታቸው ጀምሮ እያወቁ እና በትምህርት እያበለጸጉ ካላደጉ የትም አይደረሰም ። ጥቂት በራሳቸው የሚተማመኑ ተማሪዎች እንደመኖራቸው ብዙዎች ያንን አስጸያፊው መንገድ ለምን ቀረ ብለው የሚሞግቱ አሉ እና ብዙኃኑን ከጥፋት መንገድ በመመለስ ሀገርንም ለማቅናት መሰረቱ ላይ ትኩረት ቢደረግ የዝግጅታችን መልዕክት ነው ። ታምራት ዲንሳ ነኝ ጤና ይስጥልን። 
ታምራት ዲንሳ 
ኂሩት መለሰ