ለምን 60% ወጣት አፍሪቃውያን መሰደድን መረጡ?
ዓርብ፣ ጳጉሜን 1 2016መቀመጫውን ጆሐንስበርግ-ደቡብ አፍሪቃ ያደረገ እና ኢቺኮቪትስ ፋሚሊ ፋውንዴሽን የተባለው ተቋም ሰሞኑን ያወጣው ጥናት እንደሚጠቁመው ከአፍሪቃ ወጣት 60 በመቶ የሚሆነው መሠደድን ይሻል። ተቋሙ ከዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሰው ከኢትዮጵያ እስከ ደቡብ አፍሪቃ የሚገኙ በአጠቃላይ የ 16 ሐገራት ወጣቶችን ባለፉት ጥር እና የካቲት ወራት በአካል ጠይቆ ነው። በዚህም መጠይቅ 5600 ያህል ወጣቶች የተሳተፉ ሲሆን ዕድሜያቸዉም ከ18 እስከ 24 ዓመት ይደርሳል ብሏል ተቋሙ።
ለምን 60 በመቶ ያህሉ መሰደድን መረጡ?
ወጣቶቹ እንደሚሉት ከሆነ ስደትን የመረጡበት ዋና ምክንያት በሀገራቸው እንቅፋት የሆነባቸው ሙስና እና ብልሹ አሰራር ነው ተብሏል። የሀገራቸው መንግስታትም ሙስናን ለማስወገድ በበቂ ሁኔታ እየሰሩ አይደለም ብለው ያምናሉ ። ሀገራቸው ወደ «ከፋ አቅጣጫ እየተጓዘች ነው» ብለው የሚያምኑት ወጣቶች በሀገራቸው መንግሥታት ላይ ያላቸው እምነት ተመናምኗል።
በመጠይቁ እንደተሳተፉት ወጣቶች ከሆነ በሙስና የተዘፈቁ ፖለቲከኞች ላይ ጠንከር ያለ ማዕቀብ ሊጣልባቸው ይገባል። ከዚህም ሌላ ስልጣን መልቀቅን ጨምሮ፣ በአጠቃላይ የመንግስት ስርዓትን ለውጥ ወጣቶቹ ይሻሉ። ይህ ካልሆነ ቢችሉ በሚቀጥሉት አምስት አመታት ወደ ሰሜን አሜሪካ፣ ካልሆነ ደግሞ ብሪታንያ፣ፈረንሳይና ጀርመንን የመሳሰሉ የምዕራብ አዉሮጳ ሐገራት መሰደድ ፍላጎታቸው ነው።
ኢትዮጵያዊው ወጣት ስብዓት፣ ቢሳካለት ከዚህ ወደኃላ እንደማይል ገልፆልናል። « አሁን ባለው ሁኔታ መሰደድን ነው የምፈልገው። ምክንያቱ ደግሞ እኔ ያለሁት አማራ ክልል ነው። ሰላም የሌለበት ቦታ ነው። በዛ ላይ ደግሞ እንደልብ መስራት አይቻልም። ደሀ ማህበረሰብ ነው። በዛ ምክንያት ከሀገር መውጣት እንፈልጋለን»
ስብዓት 25 ዓመቱ ነው። በኮሮና እና በአካባቢው ባለው የሰላም እጦት የተነሳ የተማረው እስከ 10ኛ ክፍል ብቻ ነው። ምንም እንኳን በአሁኑ ሰዓት በግብርና ስራ ተሰማርቶ የሚገኝ ቢሆንም በማዳበሪያ እጦት ምክንያት « ምንም ውጤት የለውም» ይላል። ስለሆነም ከጓደኞቹ ጋር ስደትን የመጨረሻ አማራጫቸው አድርገው እያዩ እንደሆነ ነግሮናል።
« ለምሳሌ ወደ ካናዳ መሄድ የምትፈልጉ መመዝገብ ትችላላችሁ የሚል መረጃ መጥቶ እየተመዘገብን ነው። ቀበሌዎች ስለፈረሱ የመታወቂያ ችግር አለ ። እንጂ እየተመዘገብን ነው።»
ስደት በሞሮኮ በኩል ወደ ስፔን
የቻሉ በህጋዊ መንገድ ያልቻሉ ደግሞ በህገ ወጥ መንገድ ከሀገራቸው ወጥተው ሲሰደዱ ብዙ ጊዜ ይስተዋላል። ሮይተርስ ዜና ምንጭ ባለፈው ሳምንት እንደዘገበው በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በሞሮኮ በኩል አድርገው በመሬት አቀማመጧ የአፍሪቃ አህጉር ጫፍ ላይ የምትገኘው የስፔን ግዛት ሴኡታ ድረስ ዋኝተው ለመግባት ሞክረዋል። የስፔን መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት በቀን በአማካይ 700 ያህል ሰዎች በሌሊት ወይም በቀን ሳይቀር ዋኝተው ወደ ሴኡታ ይሰደዳሉ። ከፍተኛው ቁጥር የተመዘገበው ከሁለት ሳምንት በፊት ሲሆን በአንድ ቀን 1500 ያህል ስደተኞች ነበሩም ተብሏል። ምን ያህሉ በዚህ ስኬታማ እንደሚሆኑ የስፔን ባለስልጣት ባይገልፁም ከ150 እስከ 200 የሚደርሱ ስደተኞችን ስፔን በየቀኑ ወደ ሞሮኮ መልሳ ትልካለች። እንደ ስፔን ባለስልጣናት ከሆነ በሚቀጥሉት አራት ወራት ብቻ 150 ሺ ያህል አፍሪቃውያን ወደ ስፔን ተሰደው ይገባሉ የሚል ስጋት አላቸው።
ወደ የደቡብ አፍሪቃው ተቋም ጥናት እንመለስ ፣ ከኢትዮጵያ ባሻገር በጥናቱ የተሳተፉት ሀገራት ቦትስዋና፣ ካሜሩን፣ ቻድ፣ ኮንጎ ብራዛቪል፣ ኮት ዲቫር፣ ጋቦን፣ ጋና፣ ኬንያ፣ ማላዊ፣ ናሚቢያ፣ ናይጄሪያ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ታንዛኒያ እና ዛምቢያ ናቸው።
82 ከመቶ የሚሆኑት አፍሪቃውያን ቻይና አፍሪቃ ላይ ያላትን ተፅዕኖ ይደግፋሉ፤ 79 መቶዉ ያህሉም የዩናይትድ ስቴትስን ተፅዕኖ እንደ በጎ ይመለከታሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ከሁለት ዓመት በፊት ከተደረገው መጠይቅ ጋር ሲነፃፀር ለአፍሪቃዊነት የሚያቀነቅኑት ቁጥር በመጠኑም ቢሆን ከፍ ብሏል። ተቋሙ እንዳለው "ለህዝቡ ምንም አይነት ጥቅም ሳያስገኝ የሀገራቸው የተፈጥሮ ማዕድን ሀብት በውጭ ኩባንያዎች እየተበዘበዘ እንደሆነ 72 በመቶ ያህሉ ያምናሉ።
ስደት ወደ ካናዳ
አሊ ኢትዮጵያዊ ወጣት ነው። አፋር ክልል ውስጥ በጤና ዘርፍ ተሰማርቶ ይገኛል። ስደትን ከሚያስቡ ወጣቶች መካከል ብቻ ሳይሆን በተግባር ላይ እንደሆነ ነው የነገረን።
« እኔ ራሴ ልሄድ ነው። በጅቡቲ አድርጌ ወደ ካናዳ ለመሄድ አስቤያለሁ። ምክንያቴ በኑሮ ውድነት ምክንያት ነው። ደሞዝ በጊዜ አይሰጠንም። ጦርነትም አለ። ሰላም የለም። ከ 2015 ዓ ም አንስቶ አንድም የተቀጠረ ሰው የለም። ትምህርት ጨርሰው የተቀመጡ ብዙ ሰዎች አሉ»
አሊ ታላቅ ወንድሙ ከእሱ ቀድሞ ወደ ካናዳ እንደተሰደደ እና ህጋዊ ወረቀት አግኝቶ እየኖረ ስለሆነ አሊም ካናዳ ከገባ በኋላ እንደማይቸገር እና እንደሚሳካለት ያምናል። ሌሎች የአፋር ወጣቶችስ ? አሊ በርካታ ወጣቶች እየተሰደዱ ነው ይላል። « እኔ ራሴ የማውቃቸው ሳዑዲ አረቢያ የሄዱ አሉ። አንዱ እንደውም የመን ላይ ተመቶ የተመለሰ አለ። ዞን አምስት የሚባለው አካባቢ ሴቶች የሉም ማለት ይቻላል። ወደ ሳዑዲ አረቢያ እየተሰደዱ ነው። ወንዶቹም በሊቢያ አድርገው እየተሰደዱ ነው»
የአፍሪቃውያን ስደትን በተመለከተ በ DW ፌስ ቡክ ገፅ ላይ አስተያየታቸውን ያካፈሉን በርካታ ኢትዮጵያውያን እንደሚሉት ከሆነ ከኢትዮጵያ መሰደድ የሚፈልጉት ወጣቶች ቁጥር ከተጠቀሰው አማካይ ቁጥር ማለትም 60 በመቶ የበለጠ ሊሆን ይችላል።
ኢትዮጵያውያን የሚሰደዱበትስ ዋና ምክንያት ምን ይሆን?
ዶይቸ ቬለ በቴሌግራም ገፁ ባደረገው መጠይቅ 1300 ገደማ ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን በዋናነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶችን እና ስራ አጥነትን ይጠቅሳሉ። እነዚህም 52% ያህሉ ሲሆኑ ፖለቲካ እና የሀገሪቱ የፀጥታ ሁኔታ የሚሉት ደግሞ 44% ያህሉ ናቸው። 4 በመቶ ያህሉ ምክንያቶቹ ሌሎች ናቸው ይላሉ።
ስሙን ያልገለፀልን አንድ ወጣት እንደሚለው ደግሞ በኢትዮጵያ ስደት ይልቁንስ እየቀነሰ ነው። ለዚህ ምክንያት የሚለው ደግሞ « አሁን ላይ ስደት ብዙም ያለ አይመስለኝም። በሀገራቸው ባለው ግጭቶች አማካኝነት ፤ወጣቱ ወደ ግጭቱ ለመግባት እና ለሀገራችን መታገል ያለ ይመስለኛል። ሀገራችን አስጊ ሁኔታ ላይ ስላለች ፤ ሀገራችንን ነፃ እናወጣለን የሚል ነገር እንዳለ ነው የምሰማው።»
በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ትምህርቷን እንዳቋረች የገለፀችልን ወጣት ሲሳይ በግሏ ስደትን ባትመርጥም ምክንያቶቹ ግን ግልፅ ናቸው ትላለች። « ወጣቱ በአፍላ እድሜ ላይ ስላለ ይመስለኛው ወደ ውጪ ሀገር ተሰዶ የሚያልፍለት ስለሚመስለው ስደትን አብዛኛው ወጣት ይመርጣል። ለዛ ይመስለኛል ከዚህ ቁጥር ላይ የደረሱት። ያለው ሁኔታ ስለማይመች፣ ደስ የማይል ኑሮ ስለሆነ ያለን የውጭ ሀገር ኑሮን የምንመርጠው ለዚህ ነው ብዬ አስባለሁ።»
እንደ የአፍሪካ ልማት ባንክ መረጃ ከሆነ አፍሪቃ እድሜያቸው ከ15-35 ክልል ውስጥ የሚገኙ 420 ሚሊዮን የሚጠጉ ወጣቶች የሚኖሩባት አህጉር ስትሆን አንድ ሶስተኛ ያህሉ ሥራ አጥ ናቸው። የወጣት ህዝብ ቁጥሩም በጎርጎሮሲያኑ 2050 በእጥፍ ይጨምራል የሚል እምነት አለ።
ልደት አበበ
እሸቴ በቀለ