30ኛው የኤርትራ የነጻነት በዓል፤ ኢሳያስ አፈወርቂና ኤርትራውያን
ሰኞ፣ ግንቦት 21 201530ኛው የኤርትራ የነጻነት በዓል፤ ኢሳያስ አፈወርቂ እና ኤርትራውያን
ጊዜው 1985 ዓ/ም ነው። ወርሃ ግንቦት 16ኛው ቀን፤ ኤርትራ ከኢህኤዴግ መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት እና ከመንግስታቱ ድርጅት ባገኘችው ድጋፍ በይፋ ነጻነቷን ያወጀችበት ፤ ራሷን ችላ እንደ ሀገር የቆመችበት ዕለት ። ህግደፍ ፤ ሻዕቢያ ፣ ወይም የኤርትራ ነጻነት ግንባር ከደፈጣ ተዋጊነት እስከ ነጻ አውጭ ግንባር ደም አፋሳሹን የጦርነት ምዕራፍ በአሸናፊነት ቋጭቶ ፣ ያሰብውንም አሳክቶ የሀገር ባለቤት የሆነበት ዕለት ያለፈው ግንቦት 16 ቀን 2015 ዓ/ም እነሆ ድፍን ሰላሳ ዓመታትን አስቆጠረ። ከግንባር መሪነት ባሻገር የነጻይቱ ሀገር ፕሬዚዳንት ሆነው አንድ ያሉት የያኔው የ48 ዓመቱ ጎልማሳ ዛሬ በ78 ዓመታቸውም የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ናቸው። ኢሳያስ አፈወርቂ፤።
ጊዜው ለጉድ ይነጉዳል ። በእርግጥ የኤርትራ የነጻነት ተዋጊ ኃይል መዲናዋ አስመራን ከተቆጣጠረ 32 ዓመታት አስቆጥሯል። ይኸው ኃይል (የኤርትራ ነጻነት ተዋጊ ) ከዚያ በፊት ለሳላሳ ዓመታት ያህል በትጥቅ ትግል ላይ መቆየቱ ሲታሰብ የጊዜው ርዝመት ስሌቱን እንደሚያሰላው ሰው ሊወሰን ይችላል። አንጻራዊ ነውና ። የሆነ ሆኖ ኤርትራ እና ኤርትራውያን 30ኛውን ይፋዊ የነጻነት በዓላቸውን ባለፈው ሳምንት በተለያየ ሁኔታ ውስጥ ሆነው አክብረዋል። ዓለማቀፍ የመገናኛ ብዙኃን የኤርትራን የነጻነት ቀን የተለያየ ርዕስ ሰጥተው ዘግበውታል። ኤርትራን በተመለከተ የዘገባ ሽፋን ከሰጡቱ መካከል አንዳንዶቹ ከኤርትራ የነጻነት ቀን ይልቅ የኤርትራውያንን በሀገር ቤት እና በስደት ዓለም የሚደርስባቸውን መከራ እና እንግልት እንዲሁም የመሪዋን አምባገነንት ማጉላትን የመረጡ ይመስላል። የያኔው የነጻነት ትግል መሪ ፤ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት እርሳቸው ዛሬም በስልጣናቸው አሉ። አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ፤ በጋለ ህዝባዊ ጭብጨባ ታጅበው ባደረጉት የነጻነት ቀን ንግግራቸው ፤ «የዘንድሮው የነጻነት በዓል ሀገራዊ ትብብር ይበልጥ በተጠናከረበት ወቅት መከበሩን እና ጠላቶቻችን ላሏቸው ደግሞ አዲስ የትግል ስልት እንደሚከተሉ ። » ያስገነዘቡበት ነበር።የኤርትራ የነፃነት ቀንና የፕሬዝደንት ኢሳያስ መልዕክት
«የ2023 የነጻነት ቀናችን ነጻነታችን ሉዓላዊነታችን እና ውህደታችን ይበልጥ ደምቆ ወደ ዕድገት የምናደርገው ጉዞ ተጠናክሮ በሄደበት ታሪካዊ ወቅት ላይ ነው እያከበርን ያለነው። ይህ መልካም አጋጣሚ ነጻነታችን ፣ ሉአላዊነታችን ፣ ውህደታችን ሆነ ልማታችን የማይማይዋጥላቸው የከሰሩ ጠላቶቻችን ያረጀ መጽሐፋቸውን እየገለጡ ተንኮል የሚፈጥሩበት አጋጣሚ ስለሆነ አዲስ የትግል ዘይቤ የሚጠይቅ ነው። »
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እምብዛም ወደ የመገናኛ ብዙኃን መስኮት ብቅ ሲሉ አይታዩም ። ከስንት አንዴ እንዲህ የብሔራዊ በዓላት እና ልዩ ቃለ ምልልስ ላይ ሲከሰቱ ግን በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ጠላታችን የሚሏቸውን ምዕራባውያንን ወረፍ ሳያደርጉ አያልፉምም ይባልላቸዋል።
በዘንድሮው የኤርትራ ነጻነት ቀንም ፕሬዚዳንቱ የዩናይትድ ስቴትስን ስም ሳያነሱ አላለፉም። ከአጋሮቿ ጋር በመሆን ለሶስተኛ ጊዜ በሀገራቸው ላይ የቃጣችውን የውክልና ያሉትን ወታደራዊ ጥቃት ማክሸፍ ችለናል አሉ፤ በተለይ ያለፉትን አምስት ዓመታት ሁነት በመጥቀስ በዓሉን ለመታደም ለተሰበሰበው ህዝባቸው ሲናገሩ።
«ባለፉት አምስት አመታት አዲስ ምዕራፍ ተጀመረ ባልንበት ዋሽንግተን አዎንታዊ ክስተቶችን ለማክሸፍ ወኪሎቼ በምትላቸው ሶስት ወታደራዊ ጥቃቶችን ነው የከፈተችብን ። የመጨረሻው እና ሶስተኛው ዙር ጥቃት በተቀናጀ መከላከል በመክሸፉ ከአንዳንድ ስጋቶች ውጭ ሁኔታው አስተማሪ ሆኖ ለመጭው የሰላም ዕድል ሊከፍት ተስፋ ተጥሎበታል። ክብር ለመከላከያ ሰራዊት ይሁን። »«ከነጻ አውጭነት ወደ አምባገነንነት» 30 ዓመታት በስልጣን ላይ ኢሳያስ አፈወርቂ
ኤርትራውያኑ እንደሚሉት በእርግጥ ዕለቱ ለእነርሱ የተለየ ነው። ሲያከብሩት ግን በተለያየ ስሜት ። ከረዥም እና መራራ የትግል ጉዞ በኋላ ለተገኘ ነጻነት ስሜታቸው ልዩ እንደሆነ የሚናገሩት ነዋሪነታቸውን እዚህ ጀርመን ያደረጉት ፖለቲከኛው አቶ አሊ አማን ናቸው። ለአቶ አሊ የተገኘው ሀገራዊ የነጻነት ቀን አከባበር ልክ እንደመጀመሪያዎቹ አስር ዓመታት አይደሉም። አሁን በዓሉን ሲያስቡ ከተገኘው ሀገራዊ የነጻነት ደስታ በላይ ሀገራቸው ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ የፈጠረባቸው ሀዘን እንደሚልቅ ነው።
«እኛ የመጀመሪያዎቹን አምስት አስር ዓመታት ኤርትሪያኖች እንደ ሀገር መፍጠራችንን ትግል ደግሞ ደርግን አሸንፈን የራሳችንን ሀገር መመስረታችን በጣም እጅግ በማይገለጽበት ሁኔታ ነበር የምናከብረው ። የአሁኑ ግን ፣ አሁን ያለፈው ሃያ ዓመት ኢሳያስ አፈወርቂ ይህችን ሀገር ከተረከባት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ችግር ሃያ ዓመት በሙሉ የምከብረው በጣም በጣም በሀዘን ነው።»
የ1990ዎቹ መጀመሪያ ዓመታት የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በሁለቱ ሃገራት ካደረሰው ብርቱ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት ባሻገር ቀጣናውን ከሁለት አስርት ዓመታት ለተሻገረ ጊዜ ሰላምም ጦርነትም ያልነበረበት አካባቢ አድርጎ አሳልፏል። ለኤርትራ ደግሞ እንደ ሀገር፤ ቀጣናዊ ፣ አህጉራዊ ብሎም ዓለማቀፋዊ መገለል ያስከተለባት እንደነበር ጉዳዮን በቅርበት የሚከታተሉ ተንታኞች ይናገራሉ።
ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ይላሉ አቶ አሊ፤ ከዚህ ሁሉ በላይ ፕሬዚዳንቱ ለተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕድል አለመስጠታቸው እና ራሳቸውን ብቸኛ የሀገሪቱ ጠባቂ መሪ አድርገው መሳላቸው ለችግሮቹ መባባስ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ ባይ ናቸው።
«ኤርትራን ብታውቅ ኦፊሽያል የሆነ ተቃዋሚ የላትም እርሱ ግን (ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ) ኤርትራን እየጠበቅኳት ነው ፤ ከሌላ ኃያላን ኃይል እየጠበቅኳት ነው፤ ከየት የመጣ ኃያላን ነው? ኃያል ሀገር እኮ በአካባቢያችን የለም። »
ታዋቂዋ እንግሊዛዊት ጋዜጠኛ እና ደራሲ ሚኬላ ሮንግ የአቶ አሊን ሃሳብ የሚጋራ አስተያየት ሰጥታለች ። አቶ ኢሳያስ ባገኙት አጋጣሚ ተቀናቃኝ መስለው የታዩዋቸውን ሁሉ ዞር በማድረግ መንበረ ስልጣናቸውን ማጠናከር ላይ ማተኮራቸው ሀገሪቱ ከዴሞክራሲያዊ ስረዓት እንድትርቅ መንገድ መጥረጉን ለዶይቼ ቬለ እንግሊዘኛው ክፍል በሰጠችው ቃለ ምልልስ ተናገራለች።
ሚኬላ እንደምትለው የ911ዱ የአሜሪካው የሽብር ጥቃት ዓለማቀፉን ትኩረት ጠቅልሎ መውሰዱ ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ በሀገር ቤት ያሻቸውን እንዲያደርጉ እድል ሳይፈጥር እንዳልቀረ ነው።
« በዚያን ጊዜ ኢሳያስ በተቃርኖ ጎራ የቆሙባቸውን እና ትችት ያነሱባቸውን በርካታ ሚኒስቴሮቻቸውን ጠራርገው አስወጥተዋል። 11 ያህል ሚኒስቴሮች በቁጥጥር ስር ውለው ነበር። ከእነርሱ ውስጥ በትልቅ ደረጃ የነበሩ ሚኒስቴርም ነበሩበት ። በወቅቱ አስመራ የነበሩት ወዲያው በቁጥጥር ስር ሲውሉ ፤ ውጭ ሀገር የነበሩት ደግሞ ዳግም ላይመለሱ በዚያው ቀርተዋል። የታሰሩት እስር ቤት ቀርተዋል። እንደሰማሁት ከሆነ ከእነርሱ ውስጥ እዚያው እስር ቤት ውስጥ የሞቱም አሉ»
3oኛውን የነጻነት በዓል በደማቅ ሁኔታ ማክበራቸውን የሚናገሩት ሌላው ኤርትራዊ ነዋሪነታቸውን በአሜሪካ ያደረጉት ዶ/ር አሮን ከፈላ ናቸው ። በኤርትራ መንግስትም ይሁን በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ላይ የሚቀርቡ ክሶችን እርሳቸው አይቀበሉትም ። የትችት ፣ ወቀሳ እና ክሶች መዳረሻ አንድምታው የምዕራባውያን በኤርትራ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት መሻት ነው ይላሉ።
« ያው እንደሚታወቀው እንደመሪ የኤርትራን ትግል መርተው የመጨረሻ ምዕራፍ ካስገቡ መሪዎች ነው። ከዚህም የሁለተኛው ምዕራፍ የምንለው የኤርትራ ህላዌ እና ማንነት ጥያቄ ውስጥ የገባበት ምክንያት እንደሚታወቀው ከውጭ በሚመጣው ጫና እና ጣልቃ ገብነት ነው። እነርሱ ደግሞ የራሳቸው የሚፈልጉት አፍሪቃ ቀንድ ላይ ያላቸው ፍላጎት ኤርትራ ነጻ ሀገር ሆና ራሷን የመቻል ፍላጎት ሊጣጣም ባለመቻሉ ነው። »
በፖለቲካ ተቃዋሚዎች ፤ ተንታኞችም ሆነ ሌሎች በኤርትራ መንግስት ላይ የሚነሱ የትችት እና ተቃውሞ አስተያየቶች በርካቶች ናቸው ። የዶይቼ ቬለ የአማርኛው አገልግሎት የኤርትራ መንግስትን ሃሳብ ለማካተት ያለሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ሰሞኑን በተደጋጋሚ የፕሬዚደንት ኢሳያስ ቃል አቃባይ ወደ ሆኑት የማነ ገብረመስቀል የእጅ ስልክ ብንደውልም ሊነሳልን አልቻለም። እዚህ ጀርመን በርሊን ወደ ሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲም በተመሳሳይ ስልክ ደውለናል፤ እንዲሁ አይነሳም ።
ኤርትራ በአንድ በኩል እንደ ቻይና እና ሩስያ ካሉ የምስራቁ ዓለም ኃያላን ጋር ስሟ በተደጋጋሚ ሲነሳ ይሰማል። በሌላ በኩል ግን ከምዕራቡ ዓለም መገለል እንደደረሰባት ነው የሀገሪቱን ዓለማቀፋዊ ማህበረ ፖለቲካ እንቅስቃሴ በቅርበት የሚከታተሉት የሚናገሩት ። ጋዜጠኛ ሚኬላ እንደምትለው የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት የኤርትራን የውስጥ ጉዳይ በብዙ መልኩ ከመሰረቱ የቀየረ ነበር።
«ለነገሮች መለወጥ ዋና ምክንያት የነበረው በባድመ ጉዳይ ላይ የተቀሰቀሰው የ1991ዱ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ነው። ነገር ግን ሊሰመርበት የሚገባው ነገር ከባድመው ጦርነት ጀርባ ሌሎች ውጥረት ቀስቃሽ ነገሮች እንዳሉ ነው። የኤኮኖሚ ጉዳይ አለ፤ የሀገሪቱ የወደፊት ዕጣን የሚመለከተው ጉዳይም አንዱ ነው። »
ጦርነትም ሰላምም ሳይኖረው ሁለት አስርት ዓመታትን የተሻገረው የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን እንደመጡ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መስሎ ነበር። ነበር፤ ከህግ እና መርህ ባሻገር አንዳንዶች እንደሚሉት የሃገራቱ የግንኙነት ዳራ የግጭቱን ተዋንያን በሙሉ ያሳተፈ ባለመሆኑ እንቡጡ የተስፋ አበባ ሳይፈነዳ በዚያው መቅረቱ ይነገርለታል። የኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት ከትግራይ ኃይሎች ጋር ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ደም አፋሳሽ ጦርነት ኤርትራ የጎላ ሚና እንደነበራት በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል። ነገር ግን የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በተለይ አሜሪካ ከፍ ያለ ሚና ሳትጫወት እንዳልቀረች በተነገረለት የሰላም ጥረት መልኩን ቀይሮ ሰላም ያወረደ መስሏል። በጦርነቱ ተሳታፊ የነበረችው ኤርትራ በሰላም ሂደቱ ተሳታፊ አልነበረችም ። የፌዴራሉ መንግሥት እና ራሳቸውን የትግራይ ኃይላት ሲሉ ይጠሩ የነበሩት ተፋላሚዎች የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ስላለው ግንኙነት ከቀደመው አንጻር በይፋ የተባለለት ነገር የለም። ዐቢይ «ኢትዮጵያዊያን ያልሆኑ» ያሏቸው ማን ናቸው?
ኢትዮጵያ በበርካታ ውስጣዊ ጉዳዮች ተይዛለች። ጎሮቤት ሀገር ሱዳንም ለአጎራባቾቿ መዘዝ የሚያስከትል የእርስ በእርስ ጦርነት ላይ ናት። ኤርትራም ከምስራቁ ዓለም ኃያል ቻይና ጋር በይፋ የመሪ ለመሪ ንግግር አድርጋለች። ይህ ለዓለማቀፋዊ አሰላለፉ የሚናገር ነገር ቢኖርም ገና ግልጽ ያልሆኑ ነገሮች በርካታ ናቸው። የሆኖ ሆኖ ያነጋገርናቸው እና በውጭ የሚኖሩት በተቃርኖ ጎራ የቆሙት ኤርትራውያኑ ስለመጻዒ የሀገራቸው ዕጣ ፈንታ የተለያየ ምልከታ አላቸው ። የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባሉ አቶ አሊ አማን እንደሚሉት ኤርትራውያን አምባገነን ያሉትን ስረዓት መታገል የተስፋ ስንቃቸው ነው።
«አሁንም ደግሞ እያደረገ ያለው ጫወታ አሁን የመጨረሻ ካርድ እየተጠቀመ ነው ፤ ከቻይና እና ሩስያ ጋር ፤ ይሄ ደግሞ ግን ለእርሱ የመጨረሻ ካርድ ይመስለኛል ሳየው ። ነገር ግን የኤርትራ ህዝብ የአምባገነኑን ስረዓት በአንድነት ከታገሉ አሁንም ተስፋ አለ፤ ኤርትራ ትልቅ ሀገር ነች።»
መንግስትን የሚወግኑት ዶ/ር አሮን በበኩላቸው ምልከታቸው ሌላ ነው ። ለእርሳቸው፤ ቃል በቃል እንዳሉት « በኢትዮጵያ የወያኔ ስረዓት ማብቃቱ» ለኤርትራም ሆነ ለተቀረው የአፍሪቃ ቀንድ መረጋጋት እና ዕድገት አይነተኛ አስተዋጽዖ እንዳለው ነው።
« ለኤርትራ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪቃ ቀንድም በጣም አደገኛ ክስተት የነበረው ያው ሃያ ምናምን ዓመት የዘለቀው የTPLF የወያኔ ስረዓት ነበር ኢትዮጵያ ውስጥ እሱ አሁን የነበረው ተጽዕኖ የለም ካሁን በኋላ እንደኃይል የአፍሪቃን ቀንድ የሚበጠብጥበት ሁኔታ ስለሌለ አሁን ተግዳሮቱ ሲቀንስ ደግሞ ወደ ዕድገት ጎዳና ነው የምትገባው ግን እኔ ሁሉ ጊዜ የሚታየኝ ያው የአፍሪቃ ቀንድ ሀገሮች በኤኮኖሚም በፖለቲካም ሆነ በወታደራዊ ግንኙነት ተጣምረው በመተባበር መንፈስ ያላቸውን ጸጋ ከተጠቀሙበት በአጭር ጊዜ ውስጥ የኤኮኖሚ ዕድገት እና የሰላም ጉዞ ይጀመራል »
ምንም ተባለ ምን አንድ እውነት ግን አለ። ኤርትራ 30ኛ ዓመት የነጻነት በዓሏን ስታከብር ባልተረጋጋ ቀጣና ውስጥ ሆና ነው። ከምዕራቡ አለም ጎልቶ የሚታየው ሁለንተናዊ ጫና አሁንም ድረስ አለ። የኤርትራውያን ስደት አሁንም ድረስ መቆሚያ አላገኘም ። ስለ ኤኮኖሚዋም ቢሆን በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም ። ነገር ግን በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ውስጣዊ ሰላም ያላት ሀገር ናት፤ ኤርትራ ፤ ዓለምቀፉ ማህበረሰብ የሚተማመንባት የቀይ ባህር በር ደህንነት ጠባቂም ናት እርስዋ ። ኤርትራ ፤ ቸር እንሰንብት!
ታምራት ዲንሳ
ማንተጋፍቶት ስለሺ