ጦርነቱ የአማራ ብድር እና ቁጠባ ተቋምን ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ አክስሯል
ሐሙስ፣ ጥቅምት 18 2014የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም በአማራ ክልል እተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ ኪሳራ እንዳጋጠመው አስታወቀ። ከ60ሺህ በላይ የተቋሙ የብድርና ቁጠባ ደንበኞችም ለከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስና መፈናቀል መዳረጋቸውን ገልጿል። ደሴ የሚገኙ አንድ የተቋሙ ተፈናቃይ ደንበኛ በተለያዩ ስራዎች ተሰማርተው የነበረ ቢሆንም አሁን በተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ መና መቅረታቸውን ተናግረዋል።
የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መኮንን የለውምወሰን በጽ/ቤታቸው ለዶይቼ ቬለ እንዳሉት የሕወሓት ኃይሎች በወረራ ይዘዋቸው በነበሩ አልያም በቆዩ አካባቢዎች የሚገኙ ጽ/ቤቶችን ንብረት በከፍተኛ ሁኔታ ዘርፈዋል አልያም አውድመዋል፤ ብለዋል፡፡
አሁን ነፃ በሆኑ ከ90 በላይ በሚገኙ ጽ/ቤቶች ላይ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት መሰረት ከአንድ ቢሊዮን በላይ የሚገመት ንብረት መዘረፉን አቶ መኮንን ገልፀዋል፡፡
ተቋሙ በጦርነት ቀጠና የሚገኙና በጦርነቱ የተፈናቀሉ ከ60ሺህ በላይ ደንበኞች እንዳሉት ያመለከቱት ዋና ስራ አስፈፃሚው፣ አጠቃላይ በነዚህ ደንበኞች እጅ የሚገኝ 5 ቢሊዮን ብር ለብክነት መዳረጉንና ይህም ለተቋሙ ከፍተኛ ክስረት አንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ነፃ በሆኑ አካባቢዎች በተጠናው ጥናት መሰረት በተቋሙ ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ያስታወሱት አቶ መኮንን፣ በጠንካራ የስራ ተነሳሽነት ተቋሙ መልሶ እንዲያንሰራራ ጠንክረን እንሰራለን ብለዋል፡፡
ከደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ፣ ፀሐይ መውጫ ከተማ ተፈናቅለው በደሴ የሚገኙት የተቋሙ ደንበኛ አቶ አዳነ መላኩ በተለያዩ ሥራዎች ተሰማርተው እንደነበር አመልክተው አሁን በተፈጠረው ወቅታዊ ጉዳይ ሁሉም ነገር ባዶ ቀርቷል ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡
የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም በ1988 ዓ ም የተመሰረተ ሲሆን ካሉት 472 ጽ/ቤቶች መካከል 110 የሚሆኑት በጦርነቱ ምክንያት ስራ ያቆሙ ናቸው፡፡ ተቋሙ ከ12ሺህ 600 በላይ ሰራተኞች አሉት፡፡
ዓለምነው መኮንን
ታምራት ዲንሳ
እሸቴ በቀለ