1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዛሚቢያ እና የጋና የዕዳ ቀውስ

ዓርብ፣ መጋቢት 22 2015

የዛሚቢያና ጋና ለገጠማቸው የኢኮኖሚ ቀውስ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ብድር ለማግኘት እየጣሩ ነው።ይሁን እንጅ ከዚህ ቀደም ለነበበረባቸው ብድር ዋስትና እንደ ቻይና ካሉ አበዳሪ ሀገራት የዕዳ እፎይታ ማግኘት ቀላል አልሆነም

https://p.dw.com/p/4PY8H
IWF Logo, Schild
ምስል Maksym Yemelyanov/Zoonar/picture alliance

በቻይና እና በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አጣበቂኝ የገባው የሁለቱ ሀጋራት ብድር


የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ለዛምቢያ የ1.3 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለመስጠት ከተስማማ ሰባት ወራት በላይ ተቆጥሯል።ይሁን እንጅ የሀገሪቱ  የዕዳ ቀውሶች አሁንም አልተፈቱም። ከቅድመ ሁኔታ ጋር የመጣው ብድር ዛምቢያ  ከአበዳሪዎቿ አንዷ ከሆነችው ቻይና ጋር የብድር ዕፎይታ እንዲኖር ይጠይቃል። 
የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ጃኔት የለን  ከሁለት ወራት በፊት ሀገሪቱን በጎበኙበት ወቅት በሰጡት መግለጫ ቻይና ሂደቱን እንድታፋጥን ጠይቀዋል። በዛምቢያ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ በበኩሉ ፤ ዩናይትድ ስቴትስ በዛምቢያ የዕዳ እፎይታ ላይ ቤጂንግን ላይ ጫና ማድርጓን አቁማ በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር በሚችለው በሀገሯ የመንግስት ጉድለት ላይ ማተኮር አለባት ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
በዚሀ የተነሳ  የቻይና የዕዳ ማሻሻያ ጥያቄ  በአይኤምኤፍ ስምምነት ላይ ተጽእኖ ያመጣል የሚል ስጋት አሳድሯል።ችግሩን ለመፍታት የዛምቢያ መንግስት ኩራቱን ዋጥ አድርጎ ወደ ቻይና መቅረብ  ይኖርበታል።ይላሉ የዛምቢያ ሪፐብሊካን ፓርቲ ፕሬዝዳንት ራይት ሙሶማ ። አያይዘውም የፕሬዚዳንት ሃካይንዴ ሂቺሌማ  አሰላለፍ  በምሥራቁ ወጪ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ለመሆን ነው ሲሉ ይተቻሉ።ቻይና ለዛምቢያ ባለውለታም ናት ይላሉ።
«በዚች ሀገር ቻይና እና ሩሲያ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እንድናቆም ወይም እንድንቀንስ ታዘናል። ነገርግን እነዚህ ሀገራት በክፉም በደጉም  ከኛ ጋር ነበሩ። የምዕራባውያን ሀገራት አባቶቻችንን በቅኝ ሲገዙ ቻይና እና ሩሲያ ነበሩ ያበሉንና አብረውን ከኛ ጎን የተዋጉልን,። በመሰረተ ልማት፣ ልጆቻችንን በማስተማር መርዳታቸውን ቀጥለዋል።አሁን ቻይናና ሩሲያ ብትሄዱ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎቻችንን ያለምንም ክፍያ ሲማሩ ታገኛላችሁ።» 
የዛምቢያ የብድር ማሻሻያ  አስተባባሪው ፒተር ሙምባ እንደሚሉት በብድር እፎይታ ውይይት ዙሪያ ያለው ፖለቲካ ለብድሩ መዘግየት ትልቅ ሚና ተጫውቷል ። በG-20 ስር ያለው የጋራ የዕዳ ማሻሻያ ማዕቀፍ ሂደትም ፈተኛ  እንደገጠመው አመልክተዋል።
ሌላዋ ምዕራብ አፍሪቃዊት ሀገር ጋናም ተመሳሳይ ፈተና ገጥሟታል። የዋጋ ግሽበት  ከፍተኛ የሆነባት ጋና፤ ከ IMF 3 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ በአፋጣኝ ትፈልጋለች። በአይኤምኤፍ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት ጁሊ ኮዛክ እንደሚሉት የIMF ስራ አስፈፃሚ ቦርድ ለጋና ብድሩን ለማፅደቅ አበዳሪዎች ይፋዊ  ኮሚቴ እንዲመሰርቱ እና አስፈላጊውን የገንዘብ ማረጋገጫ በተቻለ ፍጥነት እንዲሰጡ ያስፈልጋል።ያም ሆኖ  እንደ ቻይና ያሉ የውጭ አበዳሪዎች በቀላሉ ወደዚህ ማምጣት አይቻልም።የጋና ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ አዶ  ግን ተስፋ አላቸው።
«ለፓሪስ ክለብ አባላት እና ለቻይና ህዝብ ሪፐብሊክ ስምምነት ላይ ለመድረስ  እስካሁን ላሳዩት ትብብር እና እና ይፋዊ የብድር ኮሚቴ ለማቋቋም ላደረጉት ጥረት ምስጋናየን መግለጽ እፈልጋለሁ። አይኤምኤፍ ብድሩን እንዲያፀድቅ  አስፈላጊውን የገንዘብ ማረጋገጫዎች በፍጥነት እንሚሰጡ እንጠብቃለን።» 
ጋና  ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ አበዳሪዎች ከ54 ቢሊዮን በላይ ዕዳ አለባት። 1.9 ቢሊዮን ዶላሩ ዕዳ የቻይና ነው። እንደ ዩኤስ እና ጀርመን ያሉ ሀገራት  የአይኤምኤፍ ስምምነቱን ለማስጠበቅ ለጋና ቃል ገብተዋል። ነገር ግን  ቻይና የውጭ አበዳሪዎች ኮሚቴን የምትቀላቀልበት ፍጥነት ይወስነዋል። 
ለመሆኑ  ለአይኤምኤፍ ስምምነት የቻይና ጉዳይ ለምን ወሳኝ ሆነ? የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ትሶናም ኪሊንስ አፕሎው ማብራሪያ አላቸው። 
«ቻይና ባለፉት ዓመታት በአፍሪካ ውስጥ ትልቅ ሚና ተጫውታለች። አብዛኛው የጋና እና  የአፍሪቃ ክፍል የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በቻይና ድጋፍ የተሰሩ ናቸው።,ይህም ቻይና ካሉን ዋና አጋሮች መካከል አንዷ ያደርጋታል።,ስለዚህ ከቻይና ይሁንታ ሳያገኙ የተሳካ የእዳ የዋስትናን መልሶ ማዋቀር አይችሉም።»
የጋና መንግስት የእርዳታ ቅድመ ሁኔታዎችን ለማሟላት እና ገቢን ለመጨመር አዲስ የቀረጥ አዋጅ በምክር ቤቱ ለማጽደቅ እየፈለገ ነው።ሀገሪቱ የዕዳ ክፍያ ሚዛኗን ለማስተካከል በተቻለ ፍጥነት ይህ ስምምነት ያስፈልጋታል  ያ ካልሆነ ለተራ ዜጎች የበለጠ መከራ ነው።

Ghana Präsident Nana Addo Dankwa Akufo-Addo
ምስል Anthony Anex/KEYSTONE/picture alliance
IWF Kredit, Symbolbild
ምስል Maksym Yemelyanov/Zoonar/picture alliance


ፀሀይ ጫኔ
ዮሀንስ ገብረ እግዚያብሄር