ዶክተር ቴድሮስ አድሓኖም የትግራይ ፖለቲከኞች ችግሮቻቸው በሰላም እንዲፈቱ ጥሪ አቀረቡ
ሐሙስ፣ መስከረም 2 2017የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ችግሮች በማያባብስ ሁኔታ ለውጦች ማድረጉ እንደሚቀጥል አስታወቀ። የትግራይ የፀጥታ ሐይሎች የግዚያዊ አስተዳደሩ ተግባራት የመከልከል ሐላፊነት እንደሌላቸው የአስተዳደሩ ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ተናግረዋል። አቶ ጌታቸው ይህ ያሉት የትግራይ ሐይሎች አዛዥ ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ ያለው ውዝግብ ለማርገብ ሹምሽሮች እንዲቆሙ መጠየቃቸው ተከትሎ ነው።
በሌላ በኩል የቀድሞ የህወሓት አመራር እና የአሁኑ የዓለም ጤና ድርጅት መሪው ዶክተር ቴድሮስ አድሓኖም በትግራይ ያለው የፖለቲካ ውጥረት እንዲረግብ ትላንት ባስተላለፉት መልእክት ጥሪ አቅርበዋል።
በህወሓት መሪዎች መካከል የተፈጠረው መካረር ተከትሎ እየታየ ያለው ውጥረት ለማርገብ የተባለ የተለያዩ ክልከላዎች በትግራይ ሐይሎች አዛዥ ይፋ መደረጋቸው ይታወሳል። ባለፈው ሰኞ ለመገናኛ ብዙሐን የተናገሩት የትግራይ ሐይሎች አዛዥ እና የትግራይ ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረዳ፥ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የተቆጣጠረው የህወሓት ክፍል የሚያደርጋቸው ሹምሽሮች እንዲያቆም፣ ጉባኤ ያደረገው የህወሓት ቡድንም ከስልጣን ጥያቄ እንዲቆጠብ፣ በድጋፍ ይሁን ተቃውሞ ሰልፍ ማድረግ እንዲቀር ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ይህ አነጋጋሪ ውሳኔ የግዚያዊ አስተዳደሩ የስራ እንቅስቃሴ የሚገድብ ተደርጎ በበርካቶች የተነገረለት ሲሆን በዚሁ ጉዳይ ዙርያ መግለጫ የሰጡት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ የፀጥታ ሐይሎች የአስተዳደሩ አካል እንጂ ሌላ ራሱን የቻለ ሐይል አለመሆኑ፣ ማንኛውም የአስተዳደሩ ስራ የማገዝ እንጂ የመከልከል ሐላፊነት እንደሌለው ገልፀዋል። አቶ ጌታቸው ረዳ ይህ ሐሳብ ያቀረበ አካል ራሱን ከሆነ ወገን በላይ ወስዶ ነገሮች አይወስንም ብለዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ "የትግራይ የፀጥታ ሐይሎች የሚታዩ እንቅስቃሴዎች ስርዓት ባለው መንገድ እንዲፈፀሙ የማድረግ ሐላፊነት አላቸው። ይህ ሐላፊነታቸው ለመወጣት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉም ወገን ልያግዛቸው ይገባል። ያለን መግባባት፥ ተፈጥሮ ያለው ውጥረት በማያባብስ ሁኔታ፥ ከሁሉም በላይ ደግሞ በህዝባችን ላይ ጭንቀት በማይፈጥር መንገድ ስራዎች መከወን ነው።
ከዚህ ተነስተን የጀመርናቸው ስራዎች አሉ፣ እነሱ ይቀጥላሉ። ይህ ማለት ሐሳቡ የሚያቀርብ ሐይል ራሱን ከሆነ ወገን በላይ ወስዶ፣ ነገሮች እንደዚህ ወይ በዚህ መፈፀም አለባቸው ወደሚል እየገባ ነው ማለት አይደለም" ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ፥ ችግር በማያባብስ ሁኔታ በአስተዳደር መዋቅሩ ላይ ማሻሻያዎች ማድረግ ይቀጥላል ብለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ አዲስአመት አስመልክተው ትላንት በቪድዮ የተቀረፀ መልእክት ያስተላለፉት የዓለም የጤና ድርጅት ጀነራል ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሓኖም፥ በትግራይ ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ አሳሳቢ ሲሉ ገልፀውታል።
የቀድሞ የህወሓት ከፍተኛ አመራሩ እና አሁን ላይ የዓለም የጤና ድርጅት እየመሩ ያሉት ዶክተር ቴድሮስ አድሓኖም በትግርኛ ባስተላለፉት የአዲስአመት መልእክት የትግራይ ፖለቲከኞች ችግሮቻቸው በሰላም እንዲፈቱ፣ የህዝብ አጀንዳ እንዲያስቀድሙ ጥሪ አቅርበዋል።
ዶክተር ቴድሮስ አድሓኖም "በትግራይ የሚያሳስብ ሁኔታ ተፈጥሮ እንዳለ የሚታወቅ ነው። የፈለገው ያክል የፖለቲካ ልዩነት ይኑር፣ ሰላም ሊደፈርስ አይገባም። በመግባባት እና በመነጋገር የማይፈታ ችግር የለም። ማእከላችን የህዝብ ፍላጎት ካደረግን ለሁሉም ዓይነት ልዩነት ፖለቲካዊ መፍትሔ ማድረግ ይቻላል። ሁሉም አካላት ልዩነታቸው ሊፈቱ እና የትግራይ ህዝብ ፍላጎት ሊያስቀድሙ ጥሪ አቀርባለሁ" ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ፥ በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ካሉት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር ጋር ተገናኝተ፥ በፕሪቶሪያ ውል የእስካሁን አፈፃፀም ዙርያ መምከራቸው በማሕበራዊ ትስስር ገፃቸው አመልክተዋል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ