1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ዜና፤ መስከረም 7 ቀን፤ 2017 ዓ.ም ሰኞ

ማክሰኞ፣ መስከረም 7 2017

DW Amharic የካይሮ መንግሥት ህወሓት እና ኤርትራን ማደራደር እንደሚፈልግ ተመለከተ። ግብፅና ኤርትራ ትስስራቸዉን ለማጠናከር ወታደራዊ ትብብር እና የመረጃ ልውውጥ ስምምነት ሊፈፅሙ እንደሚችል የግብፅ የዜና ምንጮች ዘገቡ። በጎንደር ከተማ ዛሬ ከማለዳ ጀምሮ በፋኖና በመንግስት ወታደሮች መካከል ውጊያ ሲካሄድ መዋሉን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ቱርክ አንካራ ላይ ሊደረግ የታቀደው ሦስተኛ ዙር ዉይይት ለሌላ ጊዜ መተላለፉን የሶማልያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ተናገሩ። ደቡብ ሱዳን በጎረቤቷ ሱዳን በኩል ወደ ውጭ ሃገር የነዳጅ ምርትን ለመላክ እና እንደገና ለማስጀመር እየሰራች መሆኑ ተነገረ።

https://p.dw.com/p/4kjNh

ግብፅና ኤርትራ የጠበቀ ትስስራቸዉን ለማጠናከር በሚጥሩበት በአሁኑ ወቅት ወታደራዊ ትብብር እና የመረጃ ልውውጥ ስምምነት ሊፈፅሙ እንደሚችል የግብፅ የዜና ምንጮች ዘገቡ።  ሁለቱ ሃገራት ፤ 11 ወራቶች በዘለቀዉ እስራኤል፤ በጋዛ ላይ በምታካሂደዉ ጦርነት፤ ከኢራን ድጋፍ የሚያገኙት የየመን አማፅያን በቀይ ባህር ላይ የስተጓጎሏቸዉን መርከቦች ለመጠበቅ የሁለትዮሽ የስምምነት እርምጃዎችን ያካትታል ተብሏል።  ሰሞኑን አስመራ ላይ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የመከሩት የግብፅ ባለስልጣናት ፤ የካይሮ መንግሥት ህወሓት እና ኤርትራን ማደራደር እንደሚፈልግ መገለፁን መና የተባለዉ የግብፅ መገናኛ ብዙሃን አክሎ ዘግቧል።  በግብፅና በኤርትራ መካከል ያለው ውይይት የተሰማዉ ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ የፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ ኤል ሲሲ መንግሥት የስለላ ተቋም ኃላፊ ጀነራል ጀማል አባስ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ባድር አብደላቲ ከኤርትራዉ የረጅም ዓመታት መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በድንገተኛ ጉብኝት አስመራ ላይ ከተገናኙ በኋላ ነዉ። የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል  ባለፈዉ ሰሞን  የትግራይ ክልልና የኤርትራ ባለስልጣናት ንግግር መጀመራቸውን በሰጡት መግለጫ መናገራቸው የሚታወስ ነዉ። የግብፁ ፕሬዚዳንት ኧል ሲሲ ወደ ስልጣን ከመጡ በዚህ 10 ዓመታት ውስጥ የኤርትራዉ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ ከፕሬዚዳንት ኧልሲሲ ጋር ለተደጋጋሚ ጊዜ ተገናኝተዋል። ኢሳያስ በካይሮ  ከአል ሲሲ ጋር ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት ባለፈዉ የካቲት ወር ላይ ነበር። ኢሳያስ ከዚህ ቀደም ብሎ ሳውዲ አረቢያ ሪያድ ላይ ኧልሲሲን አግኝተዋቸዉ እንደነበር የግብፁ መገናኛ ብዙኃን መና አስታዉሷል።  

 

በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ቱርክ አንካራ ላይ ሊደረግ የታቀደው ሦስተኛ ዙር ዉይይት ለሌላ ጊዜ መተላለፉን ሁለት የሶማልያ ከፍተኛ ባለስልጣናት መናገራቸዉ ተዘገበ። ለዛሬ ታቅዶ የነበረዉ ፤በቱርክ የሚመራዉ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ዉይይት  ላልተወሰነ ጊዜ የተላለፈዉ በሁለት ምክንያቶች እንደሆነም የሶማሊያ ባልስልጣናት ገልፀዋል።  ማንነታቸዉ እንዲነገር ካልፈለጉት ከሁለት ሶማሊያ ባለስልጣናት መካከል አንዱ ምንም አይነት መረጃ ለመናገር ፈቃድ እንደሌላቸዉ  እና፤  ቱርክ አንካራ ላይ በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ መካከል ሊደረግ የታቀደዉ ስብሰባ "ከተመድ ጠቅላላ ስብሰባ እለት ጋር በመጋጨቱ  ለሌላ ጊዜ ተላፏል» ማለታቸዉ ተዘግቧል። መረጃዉን የሰጡ ሌላው እና ሁለተኛዉ የሶማልያ ከፍተኛ ባለስልጣን በበኩላቸዉ፤ «ለስብሰባው ለመዘጋጀት በቂ ጊዜ አልነበረም» ስብሰባዉ ታቅዶ የነበረዉ ለዛሬ ማክሰኞ መስከረም 7 ነበር» ማለታቸዉ ተጠቅሷል። ኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል ያለዉን ዉጥረት ለማርገብ ባለፈዉ ሐምሌና ነሐሴ ወር ዉስጥ ቀጥተኛ ይልሆነ  ውይይቶች መካሄዳቸዉ ይታወቃል። ባለፈው ወር ይፋ በሆነዉ መተጃ መሰረት ሁለቱ ሃገራት ሦስተኛዉን ዙር ዉይይት መስከረም ወር መጀመሪያ ለማካሄድ ቀነ ቀጠሮ ይቀዉ ነበር። በዘገባዉ መሰረት ምናልባትም ሶማልያ የስብሰባዉን ቀጠሮ ሌላ ቀን እንዲዛወር ሳትጠይቅ አልቀረችም።    
 

በጎንደር ከተማ ዛሬ ከማለዳ ጀምሮ በፋኖና በመንግስት ወታደሮች መካከል ውጊያ ሲካሄድ መዋሉን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የጎንደር ከተማ ነዋሪ እንደገለፁትከጠዋት 12 ሰዓት ጀምሮ በከባድ መሳሪያ የታገዘ ውጊያ በተለይም “ገንፎ ቁጭ” በተባለ የከተማው ክፍል ላይ ሲካሄድ እንደነበር አመልክተዋል።  ዛሬ ከቀኑ 8 ሰዓት ተኩል ጀምሮ የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ ግን አሁን የተኩስ ድምፅ እንደማይሰማ እኚህ አስተያየት ሰጪ ተናግረዋል፡፡ ሌላ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው ዝናቡ ካባራ በኋላም ቢሆን የከባድ መሳሪያዎች ድምፅ እየተሰማ እንደነበር ነዉ የተናገሩት፡፡ በከተማዋ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ የለም ሲሉ  የከተማዋ ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ  ገልፀዋል፡፡ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ዮሐንስ፣ ሽንፋ፣ ኮኪትና ገንዳ ውኃ ዙሪያ በመንግስትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ተመሳሳይ ውጊያ ሲካሄድ እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል፡፡

 

አንጋፋው መምህር እና ፖለቲካኛ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በጠና ታመዉ በህክምና ሲከታተሉ እንደነበር ተመልክቷል። የፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን በሞት መለየት በማህበራዊ መገናኛ ገጻቸዉ ላይ ዛሬ ይፋ ያደረጉት  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ  «ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በኢትዮዽያ ገንቢ የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ የሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ምልክት ነበሩ» በማለት ሐዘናቸውን ገልፀዋል።  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ «ረዘም ላለ ጊዜ በህክምና ሲረዱ ቆይተው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ስሰማ ከልብ አዝኛለሁ» ሲሉም ጽፈዋል። በ 1942  ዓ.ም በደቡብ ኢትዮጵያ ሃድያ ሾኔ ከተማ አቅራቢያ የተወለዱት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን እዚያው አካባቢ ካጠናቀቁ በኋላ፤ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ መካነ አዕምሮ በሥነ ሕይወት አጠናቀዋል። ሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በዩናይትድ ስቴትስ ተምረዉ መመረቃቸዉን የህይወት ታሪካቸዉ ያሳያል። ከ 1978 እስከ 1982 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕይወት ትምህርት ክፍል ኃላፊ ሆነውም አገልግለዋል።  ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በ1983 ወደ "ተግባራዊ ፖለቲካ" ገብተዉ የሽግግር መንግሥቱ አባል እንደነበሩ፣ በወቅቱ የትምህርት ሚኒስትር ድኤታ ሆነው ለጥቂት ጊዜ ማገልገላቸውም የህይወት ታሪካቸዉ ያሳያል።  ፕሮፌሰር በየነ ጳጥሮስ በ1983 ዓ.ም ጀምሮ በሰላማዊ ትግል የድርሻቸውን ያበረከቱ እና የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር ሆነው ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ ናቸዉ።   

 

ደቡብ ሱዳን በጎረቤቷ ሱዳን በኩል ወደ ውጭ ሃገር የነዳጅ ምርትን ለመላክ እና እንደገና ለማስጀመር እየሰራች መሆኑ ተነገረ። ሮይተርስ የዜና ወኪል  የደቡብ ሱዳን የገንዘብ ሚኒስትርን እና የፕሬዝዳንቱን ጽህፈት ቤት ገለጾ እንደዘገበዉ፤ ሁለቱ ሃገራት የደቡብ ሱዳንን የነዳጅ ምርት ለዉጭ ገበያ መላክን ለማስጀመር በጥድፍያ እየሰሩ ነዉ። 
ከደቡብ ሱዳን፤ በሱዳን በኩል ለዉጭ ገበያ ይቀርብ የነበረዉ ድፍድፍ ነዳጅ ፣ መላክ የቆመዉ ምርቱን ማስተላለፍያ ማመላለሻ ቧንቧ በሱዳን ጦርና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል በተቀሰቀሰዉ ጦርነት ምክንያት በደረሰበት ጉዳት መሆኑ ተጠቅሷል።  
ሮይተርስ የዜና ወኪል  የደቡብ ሱዳን የገንዘብ ሚኒስትርን እና የፕሬዝዳንቱን ጽህፈት ቤት ትናንት ሰኞ ምሽት የሰጡትን መግለጫ ጠቅሶ እንደዘገበዉ፤ በመጪዎቹ ሳምንታት ሱዳንን የሚጎበኙት የደቡብ ሱዳን መሃንዲሶች  በሱዳን የሚገኘዉ የደቡብ ሱዳንን ድፍድፍ የሚቆጣጠረዉ ተቋም ስራ ለመጀመር እና የነዳጅ ምርትን ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን በአካል ተገኝተዉ ይገመግማሉ።  በጦርነቱ ምክንያት ደቡብ ሱዳን የነዳጅ ድፍድፍ መላክ ከማቋረጥዋ በፊት ፤ በቀን 150,000 በርሜል ድፍድፍ በሱዳን በኩል ወደ ውጭ ሃገራት ትልክ እንደነበር ይታወሳል።  

 

ባሳለፍነዉ ሳምንት መጨረሻ በማዕከላዊ አዉሮጳ ሃገራት በጣለ ከባድ ዝናብ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ የሟቾች ቁጥር 16 መድረሱ ተመለከተ።  ከፍተኛ ዝናብ ያስከተለው የወንዞች ውኃ ሙላት፤ ግድቦችን እና ድልድዮችን አልፎ፤ አነስተኛ ከተሞችን መዋጡን እና መሰረተ ልማቶችን ማፈራረሱን ሶሽየትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ በተለይ ፖላንድ እና ቼክ ሪፐብሊክ ድንበር አቅራቢያ የሚገኙ አካባቢዎች በአደጋው ክፉኛ መጎዳታቸዉ ነዉ የተመለከተዉ። የነፍስ አድን ሰራተኞች እና ወታደሮች የጎርፍ መጥለቅለቅ በደረሰባቸዉ አካባቢዎች በነፍስ አድን ስራ ላይ ተሰማርተዋል፡፡ በአደጋው የመኖርያ ቤቶች ፈራርሰዋል፤ ትምህርት ቤቶች እና የጤና ተቋማት ተዘግተዋል፤  የስልክ፤ የውኃ እና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋርጧል።  ፖላንድ የድንበር ላይ የምትገኘዉ እና በዉኃ ሙላት የተጥለቀለቀችዉ ከሎደዝኮ ከተማ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በግማሽ ተቋርጧል፡፡ ከተማዋን የሸፈነዉ የዉኃ ሙላት እየቀነሰ ቢሆንም የመጠጥ ዉኃን ጨምሮ አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልግ፤ የከተማዋ ከንቲባ መናገራቸዉ ተመልክቷል። የፖላንድ መንግሥት የመጥለቅለቅ አደጋ በደረሰባቸዉ አካባቢዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዉጇል፤ የርዳታ ገንዘብም መድቧል። በሳምንቱ መጨረሻ በማዕከላዊ አዉሮጳ የዘነበዉ ዝናብ ያስከተለዉ የመጥለቅለቅ አደጋ ፤ በተለይ በኦስትሪያ እና ሮማኒያ በርካታ የሰው ህይወት ያለፈባቸው ሀገራት ናቸዉ። የሃገራቱ ባለሥልጣናት የሟቾች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል እየገለፁ ነዉ። በማዕከላዊ አዉሮጳ ይህን መሰል ከፍተኛ አደጋ ሲከሰት ከሁለት አስርተ ዓመታት ወዲህ ይህ ለመጀመርያዉ ጊዜ ነዉ። 

 

የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላዲሚር ፑቲን ከዩክሬይን ጋር የሚያካሂዱት ጦርነት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የጦር ሠራዊታቸዉን ቁጥር ለሦስተኛ ጊዜ ማሳደጋቸዉ ተሰማ። በፑቲን ዉሳኔ መሰረት ከታህሳስ ወር ጀምሮ 1.5 ሚሊዮን ወታደሮችን ጨምሮ በጦር ሰራዊት ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰዎች ቁጥር ወደ 2.4 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል። ፑቲን ባሳለፍነዉ ታኅሣሥ ወር፣ 1.3 ሚሊዮን ወታደሮችን ጨምሮ የጦር ኃይሉን ወደ 2.2 ሚሊዮን ከፍ ማድረጋቸዉን የፈረንሳይ ዜና ወኪል አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ አስታዉሷል። ጦርነቱ በተቀሰቀሰበት በጎርጎረሳዉያኑ 2022 ዓመት በሩሲያ የነበሯት ወታደሮች ቁጥር አንድ ሚሊዮን ገደማ የነበረ እና ይህ ቁጥር አሁን ካለዉ የሩስያ ወታደራዊ ኃይል ጋር ሲነጻፀር 50 በመቶ መጨመሩ ተመልክቷል። 

አዜብ ታደሰ 

ፀሐይ ጫኔ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።