1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእስራኤል ሃማስ ግጭት እና አፍሪቃ

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 10 2016

አፍሪቃ ውስጥ በርካቶች በእስራኤል እና በሃማስ ታጣቂ ኃይል መካከል ተኩስ ቆሞ ውይይት እንዲካሄድ እያሳሰቡ ነው። አንጎላ፤ ኬንያ፤ ጊኒ ቢሳው፤ እና ደቡብ አፍሪቃ ጥቃቱን በተመለከተ ስጋታቸውን የገለጹ እና የቀጠለውን እስራኤል ፍልስጤም ግጭትም በይፋ ካወገዙ የአፍሪቃ ሃገራት መካከል ናቸው።

https://p.dw.com/p/4Xp1t
ፎቶ፤ ለውጊያ የተዘጋጀው የእስራኤል የምድር መከላከያ ኃይል
በመካከለኛው ምሥራቅ የተባባሰው ግጭት የመላውን ዓለም ትኩረት ስቧል። ፎቶ፤ ለውጊያ የተዘጋጀው የእስራኤል የምድር መከላከያ ኃይል ምስል Jim Hollander/newscom/picture alliance

የእስራኤል ሃማስ ግጭት እና አፍሪቃ

አፍሪቃ ውስጥ በርካቶች በእስራኤል እና በሃማስ ታጣቂ ኃይል መካከል ተኩስ ቆሞ ውይይት እንዲካሄድ እያሳሰቡ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ፣ የአውሮጳ ሕብረት፤ በጀርመን እና በሌሎችም ሃገራት በአሸባሪነት የተፈረጀው ሃማስ ድንገተኛ የሮኬት ጥቃት እስራኤል ግዛት ውስጥ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰ በኋላ የእስራኤል የመከላከያ ጦር ጋዛ ላይ አጠናክሮ የቀጠለው የአጸፋ ጥቃት የዓለምን ትኩረት ስቧል። የጥቃቱ መባባስ በርካታ ሲቪሎችን ለአደጋ በማጋለጡም ሰላማዊ ዜጎች ተጨማሪ ከለላ እንዲያገኙ ማሳሰቢያዎች ተደጋግመው ይሰማሉ። የአፍሪቃ ሕብረት እና ደቡብ አፍሪቃ በይፋ ጥቃት ይቁም በማለት መልእክት አስተላልፈዋል። ምንም እንኳን የመላው አፍሪቃ ሃገራት ሕብረት የሆነው ድርጅት ድምጹን በግልፅ ቢያሰማም የየሃገራቱ አስተያየትና ምላሽ ግን ከእስራኤል ጋር እንዳላቸው ትስስርና ግንኙነት መለያየቱ ይታያል።

የኬንያ ፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ ሃማስ እስራኤል ላይ ያደረሰውን የሽብር ጥቃት በጠንካራ ቃላት አውግዘው፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሽብር ወንጀል ያሉትን ጥቃት በፈጸሙ፣ ባቀነባበሩ፣ በገንዘብ በረዱ እና በደጋፊዎች ላይ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል። ፕሬዝደንት ሩቶ በቀድሞ ትዊተር አሁን ኤክስ ተብሎ በሚጠራው የማኅበራዊ መገናኛ ገጻቸው በጻፉት መልእክት፤ «ኬንያ ከእስራኤል ጎን ከተባበረው ከቀሪው ዓለም ጋር መሆኗን፤ በማያሻማ መልኩ ሽብርን እና በሀገሪቱ ንጹሐን ላይ የሚፈጸም ጥቃትን እንደምታወግዝ» አስታውቀዋል። ዶቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው ላይቤሪያዊ የታሪክ ምሁር ሳሙኤል ኪፕቶ ኬንያ እና እስራኤል ጠንካራ የሁለትዮች ግንኙነት ያላቸው ሃገራት መሆናቸውን ነው ያመለከቱት።

ፎቶ ከማኅደር፤ የኬንያ ፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ
ኬንያ ከእስራኤል ጋር ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ የትብብር ወዳጅነት ያላት ሀገር መሆኗ ይነገርላታል። ፎቶ ከማኅደር፤ የኬንያ ፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ ምስል Khalil Senosi/AP/picture alliance

አንጎላ፤ ኬንያ፤ ጊኒ ቢሳው፤ እና ደቡብ አፍሪቃ ጥቃቱን በተመለከተ ስጋታቸውን የገለጹ እና የቀጠለውን እስራኤል ፍልስጤም ግጭትም በይፋ ካወገዙ የአፍሪቃ ሃገራት መካከል ናቸው። እነዚህ ሃገራት ባስቸኳይ ግጭቱ ቆሞ ውይይት ይካሄድ በማለት ሁለቱንም ወገን ጠይቀዋል። የአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በበኩላቸው፤ የፍልስጤም ሕብዝን መሠረታዊ መብቶች በተለይም ነጻ እና ሉአላዊ ሀገር መሆንን መንፈግ፤ በእስራኤል ፍልስጤም መካከል ውጥረቱ ቋሚ እንዲሆን ዋና ምክንያት ነው» ብለዋል። ሊቀመንበሩ አክለውም ሁለቱም ወገኖች ባስቸኳይ ጥቃት አቁመው፤ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመለሱም ተማጽኖ አቅርበዋል።

«ሃገራት ለአንድ ወገን ማድላት የለባቸውም»

ካምፓላ ዩጋንዳ የሚገኙት የመብት ተሟጋች  ኢብራሂም ሴንዳውላ በመካከለኛው ምሥራቅ በሚታየው ግጭት ሃገራት ለአንድ ወገን የሚያደሉ ከሆነ ችግሩን ይበልጥ ያባብሱት እንደሆነ እንጂ መፍትሄ አያስገኝም። በእስራኤል ፍልስጤም መካከል ሰላም እንዲወርድ መፍትሄ እንደመፈለግ ለአንድ ወገን ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ በይፋ የሚናገሩ ሃገራትን አቋምም ያለመታደል ብለውታል። ሌላኛው አፍሪቃዊ ፒተር ካሙ በሲቪሎች ላይ አሁን ከደረሰው የባሰ ጥቃት ሊደርስ እንደሚችል ስጋት አላቸው። እንደ ፒተር ካሙ አስተያየትም አብዛኞቹ የአፍሪቃ ሃገራት በጉዳዩ ላይ ሃሳብ ከመሰንዘር መታቀባቸው በሃይማኖት ምክንያት ባለው ዝንባሌ ሳይሆን አይቀርም።

የተኩስ አቁም እና ለሁለት መንግሥታት መፍትሄ የቀረበው ጥሪ

የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም እንዲሰፍን ተቀናቃኞቹ ኃይሎች ለሁለት መንግሥታት ህልውና ዳግም ወደ ድርድር እንዲመለሱ ጠይቀዋል። የዩጋንዳ ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቪኒም በበኩላቸው የእስራኤል ፍልስጤም ግጭት ዳግም ማገርሸቱ የሚያሳዝን መሆኑን አመልክተው፤ ለምንድነው ሁለቱም ወገኖች የሁለት መንግሥታትን መፍትሄ ተግባራዊ የማያደርጉት?» በማለት ጠይቀዋል። ሊወገዝ የሚገባውንም ሲገልጹ፣« ሊወገዝ የሚገባው በተለይ ሲቪሎችን እና ተዋጊ ያልሆኑ ወገኖችን ኢላማ ማድረግ ነው» በማለት አውግዘዋል። የጊኒ ቢሳው ፕሬዝደንት ዑማሮ ሲሶኮ ኤምባሎም እንዲሁ ለሚደርሰው ጥቃት እና ለጠፋው የሰው ሕይወት ሃዘናቸውን በመግለጽ በጋዛ መስመር ተኩስ እንዲቆም የበኩላቸውን ጥሪ አቅርበዋል። «ጊኒቢሳው የሰላም ሀገር ናት» ያሉት ኢምባሎ፤ የጦርነትን አስከፊነት በመረዳትም ጋዛ አካባቢ በሚታየው ከልብ ማዘናቸውን ገልጸዋል። የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ ሀገራቸው ግጭቶችን በመፍታት በኩል ያላትን ተሞክሮ በመጥቀስ፤ የእስራኤል ፍልስጤም ግጭት እልባት እንዲያገኝ በሽምግልና ለመርዳት ዝግጁ ነኝ ብለዋል። ራማፎሳ ባለፈው ሳምንት ይኽን አስመልክተው ባስተላለፉት መልእክት በአስቸኳይ እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በመካከለኛው ምሥራቅ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው እንዲደርስ «ሰብአዊ መተላለፊያ» እንዲከፈት ጥሪ አቅርበዋል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱትም በያዝነው ሳምንት መጨረሻ ካይሮ ግብፅ ላይ የእስራኤል ጋዛ ግጭትን በሚመለከት በሚካሄደው ጉባኤ እንደሚሳተፉ ጽሕፈት ቤታቸው አስታውቋል። የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝደንት ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫም፤ ፕሬዝደንቱ ለበርካቶች ሞት፤ መፈናቀል እና ሰብአዊ ቀውስ ምክንያት በሆነው ሲቪሎች ላይ በሚደርስ ጥቃት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማቸው አመልክቶ፤ ደቡብ አፍሪቃ በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ዓለም አቀፍ ጥረት ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኗን አስታውቋል። በመላው አፍሪቃ አሁን በእስራኤል እና ፍልስጤም ግዛት በመካሄድ ላይ ያለው ውጊያ በሁለቱ ወገኖች መካከል የኖረው ግጭት ቀጣይ ክልፍ እንጂ እስራኤል ጥቃት ካደረሰባት ታጣቂ ቡድን ሃማስ ጋር በተናጠል የምታካሂደው ተደርጎ አልታየም። እንዲህ ያለው ግንዛቤም ይመስላል የአፍሪቃ ሃገራት በጉዳዩ ላይ አንድ አይነት አቋም እንዳይኖራቸው ያደረገው በሚል የሚገምቱ ጥቂት አይደሉም።  

ፎቶ ከማኅደር፤ የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ
ደቡብ አፍሪቃ በእስራኤል ፍልስጤም መካከል የቀጠለውን ግጭት በሽምግልና ለመፍታት እንደምትፈልግ አስታውቃለች።ፎቶ ከማኅደር፤ የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳምስል Stanislav Krasilnikov/TASS/dpa/picture alliance

ሸዋዬ ለገሠ/አይዛክ ሙጋቤ

አዜብ ታደሰ