የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ክልል እየወጡ ነው ተባለ
ዓርብ፣ ጥር 12 2015ትግራይ ክልል ዓድዋ፣ አክሱም እና ሽረ አካባቢዎች ውስጥ የነበሩ የኤርትራ ወታደሮች አካባቢውን ለቅቀው እየወጡ መሆኑን ነዋሪዎች ገለፁ። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን ደግፈው በመዋጋት ወደ ትግራይ ክልል የገቡት እነዚህ የኤርትራ ወታደሮች ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች መውጣት የጀመሩት ከትናንት በስትያ መሆኑ ተገልጧል። ዛሬ ደግሞ በብዛት መውጣት መቀጠላቸውን የመቐለው ዘጋቢያችን ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ ከዓድዋ እና ሽረ ከተሞች ያነጋገርናቸው የዓይንእማኞች ተናግረዋል።
ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ አንድ የዓድዋ ከተማ ነዋሪ የኤርትራ ጦር ከዓድዋ ከተማ፣ ፈላፍል እና እንዳባገሪማ የተባሉ አካባቢዎች መውጣት የጀመሩት ከትናንት በስትያ መሆኑን የነገሩን ተናግረዋል። በዕለቱ « ሠላሳ ሰባት የሻዕቢያ ሰራዊትን የጫኑ መኪኖች ወደ ራማ አቅጣጫ ሄደዋል» ም ብለዋል የዐይን እማኙ። ትናንት ሌሊት፣ ዛሬ ንጋት እና ጠዋትን ጨምሮ በተለያዩ ግዙፍ መኪኖች የተጫኑ የኤርትራ ወታደሮች፣ የኤርትራ ሠንደቅ ዐላማን እያውለበለቡ፣ ዘፈኖች እና መፈክሮች እያሰሙ ወደ አክሱም አቅጣጫ እየተጓዙ አርፍደዋል በማለትም አክለዋል። የኤርትራ ጦር ሲወጣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና ፌደራል ፖሊስ በከተማዋ ጎዳናዎች ጥበቃ ሲያደርጉ መመልከታቸውን የመረጃ ምንጫችን ጨምረው ገልፀውልናል።
ከሽረ ከተማ ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው «የኤርትራ ጦር ይወጣል ተብሎ ዛሬ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ጀምሮ አውራ ጎዳናዎች ሁሉ ተዘግተው ነው ያሉት» ብለውናል። ተኽሊት የተባለ የሽረ ከተማ ነዋሪ የኢትዮጵያ ወታደሮች በሽረ ከተማ ጎዳናዎች ማንም እንዳይንቀሳቀስ ከልክለዋል፣ በከተማዋ አንድ አቅጣጫ ከነበርክ አስፓልት ተሻግሮ ወደ ሌላ መንደር ለመሄድ እንኳን አይቻልም» ያሉ ሲሆን፥ በአክሱም አቅጣጫ የመጡትን ጨምሮ በየአካባቢው የነበሩ በርካታ የኤርትራ ወታደሮች ከተማዋን አቋርጠው ወደ ዓዲዳዕሮ አቅጣጫ እየሄዱ መሆናቸውን ገልፀውልናል።
ያነጋገርናቸው የዓድዋ እና ሽረ ከተማ ነዋሪዎች በመኪና ከተጫኑ ወታደሮች በተጨማሪ በርካታ ታንኮች፣ መድፎች እና ሌሎች የእግረኛ ጦር ክፍል ተሽከርካሪዎችም ከሰራዊቱ ጋር አብረው እየወጡ መሆኑ ነግረውናል።
የኢትዮጵያ መንግስት እና ሕወሓት በደረሱት የሰላም ስምምነት መሰረት በጦርነቱ ወደ ትግራይ የገቡ የውጭ ኃይላት ከክልሉ ሊወጡ ይጠበቃል። በኤርትራ ጦር እንቅስቃሴ ዙርያ ከሕወሓት እንዲሁም ከኢትዮጵያ እና ኤርትራ መንግስታት በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሰ