የኢትዮ-ሶማሊያ ዉዝግብ፣ የምስራቅ አፍሪቃ ቀውስ ሌላው ስጋት
ሐሙስ፣ ነሐሴ 23 2016ኢትዮጵያ እና ራሷን የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ ብላ የምትጠራዉ ግዛት ባለፈዉ ታሕሳስ ማብቂያ የተፈራረሙት የወደብ ኮንትራት የመግባቢያ ስምምነት ከሶማሊያ ፌደራል ሪፐብሊክ ጠንካራ ተቃዉሞ ገጥሞታል።የኢትዮጵያና የሶማሊላንድ ስምምነትን አጥብቃ ያወገዘችዉ ሶማሊያ ግብፅን ከመሳሰሉ ሐገራት ጋር የጀመረችዉ ወዳጅነት በቀጣናው ችግሮችን እየመዘዘ ነው፡፡ግብፅ ባለፈዉ ማክሰኞ ለሶማሊያ ጦር መሳሪያ መላኳ ደግሞ ዉዝግብና ሥጋቱን አንሮታል።
የኢትዮ-ሶማሊላንድ ስምምነት እንደ መዘዝ
ትውልደ ኤርትራዊው የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ተንታኝ አቶ አብዱራሃማን ሴይድ ኢትዮጵያ ራስ ገዝ ከሆነችውና የሶማሊያ ሪፐብልክ መንግስት የራሴ አካል ከሚለው ሶማሊላንድ ጋር ስምምነት ማኖሯ ወዲያውኑ ውዝግብ ባያስነሳም፤ አሁን ላይ ደግሞ የግብጽ ወታደራዊ ትጥቅ ሶማሊያ መድረስ መጀመሩ የስምምነቱ መዘዝ ከፍ ወዳለ ስጋት ለመሸጋገሩ ማሳያ ነው ብለውታል፡፡ “ስምምነቱ ሌሎች ሃይሎች ወደ ቀጣናው እንዲመጡ ጋብዟል፡፡ ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲና ኢኮኖሚው ወዳጅ ቱርክ ቀድማ ሶማሊያ መድረሷ ስጋትን ባይፈጥርም፤ አሁን ላይ በጂኦ ፖለቲካውም ሆነ በአባይ ወንዝ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር የምትወዛገበው ግብጽ ታጥቃም ይሁን ለማስታጠቅ ሶማሊያ መድረሷ እንደ ጥሮ አጋጣሚ ስትጠብቀው የኖረች ነዉ” ብለውታልም፡፡
እንደ ፖለቲካ ተንታኙ አስተያየት ምናልባትም ግብጽ ከዚህ በፊት ለአስር ኣመታት እና ከዚያ በላይ ከኢትዮጵያ ጋር ከስምምነት ላይ ያልደረሱበትን የአባይ ጉዳይ በጦርነት አማራጭ ለመፍታት ፍላጎት የምታሳድር ከሆነ ሁኔታውን እንደ እድል ልትጠቀምበት ትችላለች፡፡ ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ምላሽ ሊሆን ይገባል ያሉት፡ “ኢትዮጵያ የተፈራረመችውን ስምምነት በመተው በቱርክ የተጀመረውን የእጅ አዙር ድርድር በቀጥታ ሶማሊያ ጋር በማጠናከር ወደ ቀጣናው የሚጋበዙትን አገራት ማጠፍ አለባት” ብለዋል፡፡
ስምምነቱ ከዓለማቀፍ ህግ ጋር ስቃኝ
የዓለማቀፍ ህግ አዋቂና ተንታኝ አቶ ባይሳ ዋቅዎያ ግን በዚህ የሚስማሙ አይመስልም፡፡ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችው የወደብ ስምምነት በዓለም አዲስም ያልሆነና የጣሰውም ዓለማቀፍ ህግ የለውም ብለዋል፡፡ “ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የገባችውን ስምምነት ምናልባት ለጊዜው የመጣ ልትል ትችል ይሆናል እንጂ ስህተት ብሎ መጥራት ከባድ ነው፡፡ የዓለማቀፍ ህግ የሚባለው አንጻራዊ ነው፡፡ ባለቤቶቹም መንግስታት ናቸው፡፡ ህጉን ከፈረሙት ካጸደቁት ደግሞ ኢትዮጵያ አንዷ ናት፡፡ ህግ ተጣሰ የሚባለው በተጣሰው ህግ ቀጪ ስኖር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችው ስምምነት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ነገር ደረጉ በርካቶች ናቸው” ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከግዛቷ ጋር ያደረገችው ስምምነት አዲስ ነገር ነውን?
ለዚህም ማሳያ ያሉትን ሲያቀርቡ፤ “የሶማሊላንድ ፓስፖርትን እውቅና ሰጥተው ያለቪዛ ዜጎቿን የሚያጓጉዙ አገራት በአውሮፓ አሉ፡፡ ግዛቷ በያራት ዓመቱ የምታከናውነውን ምርጫ ፍጹም ዴሞክራሲያዊ ብለው ታዛቢዎች የሚልኩ የአፍሪካ አገራትም አሉ፡፡ የአገር ሉዓላቂነት ማክበር እንደተጠበቀ ሆኖ ሌላው መብተ ተጥሷል ስል ያንን መቀበልም ግድ ነው፡፡ ለምሳሌም ኤርትራ መብቴ ተጥሷል ብላ ከኢትዮጵያ ስትገነጠል እንደደገፏት ማለት ነው፡፡ እናም አዲስ ነገር ለም” ብለዋል የዓለማቀፍ ህግ ባለሙያው፡፡
አቶ ባይሳ በተግባር የሚታይ ያሉት እውነታም፤ “የግብጽ ከሶማሊያ ጋር ወዳጅነት ፈጥራ የጦር መሳሪያ ማቅረብ ህዳሴ ግድብ ላይ የተሸነፈችበትን የሙግት ግብግብ በዚህ በኩል ትቀጥላለች ብሎ መጠበቅ ትክክልም ነበር” ነው ያሉት፡፡
የፖለቲካል ተንታኙ አቶ አብዱራሃማን ሰኢድም ሁለቱ አገራት በተቻላቸው መጠን አውዳሚ የሆነውን ጦርነትን ማስቀረት የሚቻልበትን መንገድ መፈለግ እንዳለባቸው መክረዋል፡፡
ስዩም ጌቱ
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ስለሺ