1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የባንክ ሒሳብ ዳግም ታገደ

ዓርብ፣ መስከረም 10 2017

ከከሳሽ ጠበቆች መካከል አንደኛው ጠበቃ አያሌው ቢታኔ በተቋሙ ውሳኔዎች እና የባንክ ሒሳብ ላይ ትናንት ዳግም የፍርድ ቤት የእግድ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ማስደረጋቸውን ተናግረዋል። ከሳሾች እንደሚሉት ይህንን ተከትሎ ገንዘብ የማሸሽ ጥርጣሬ አለን በሚል ለፍርድ ቤት አቤቱታ ካቀረቡባቸው ምክንያቶች አንዱ ይህ ነው።

https://p.dw.com/p/4kuff
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አርማ
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አርማ

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የባንክ ሒሳብ ዳግም ታገደ

በእነ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በኩል እና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል በሆኑ ጥቂት ፌደሬሽኖች በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ላይ ያልተገባ ጠቅላላ ጉባዔን ማድረግ፣ ውሳኔዎችን ማሳለፍ፣ ከፓሪስ ኦሊምፒክ ጋር በተያያዘ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እንዲሁም ከፍተኛ የሀብት ብክነት ተፈጽሟል የሚሉ ክሶች ቀርባው ባለፈው ሳምንት የተቋሙ ጉቤኤዎች እና የባንክ ሒሳቦች ታግደው ነበር። የስፖርት ነክ ጉዳዮች በመደበኛ ፍርድ ቤት እንደማይታዩ ጠቅሶ በሚደረገው ነገር ሀገር እንዳትቀጣ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ሲል አሳስቦ የነበረው የኢትዮጵያ ኦሉምፒክ ኮሚቴ በዚህ ላይ አቤቱታ በማቅረብ እግዱን ያስነሳው በማግስቱ ነበር።

በዚህ ላይ ቅሬታ አድሮብናል ያሉት የከሳሽ ጠበቆች ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤቱታ ማቅረባቸውን የገለፁልን ከከሳሽ ጠበቆች መካከል አንደኛው ጠበቃ አያሌው ቢታኔ በተቋሙ ውሳኔዎች እና የባንክ ሒሳብ ላይ ትናንት ዳግም የፍርድ ቤት የእግድ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ማስደረጋቸውን ተናግረዋል። "ፍርድ ቤቱ አቤቱታችንን ሰምቶ እና መርምሮ ከሠራተኛ ደሞዝ መክፈል በቀር ሌሎቹ ገንዘቦች እንዳይንቀሳቀሱ ትዕዛዝ እንዲሰጥልን የሚል አቤቱታ አቀረብን፣ ፍርድ ቤቱም አቤቱታችንን ሰምቶ የባንክ እግድ እንዲሁም ደግሞ ጠቅላላ ጉባኤው ታግዶ ይቆይ የሚል ትእዛዝ ሰጥቷል"።
በሌላ በኩል ክስ የቀረበበት ወይም መልስ ሰጪው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ ለተሳተፉ አትሌቶች እና የቡድኑ አባላት ትናንት የእዉቅና እና  ሽልማት ሥነ ሥርዓት አካሂዷል። ከሳሾች እንደሚሉት ይህንን ተከትሎ ገንዘብ የማሸሽ ጥርጣሬ አለን በሚል ለፍርድ ቤት አቤቱታ ካቀረቡባቸው ምክንያቶች አንዱ ይህ ነው።


"አትሌቶቹ ሽልማታቸውን በማናቸውም ጊዜ አያጡትም። ዋናው እኛ ፍትሕ እና እውነት ሊዳኝ ይገባል፣ እውነት ሊወጣ ይገባል፣ የኢትዮጵያ ስፖርት ዘርፍ ሊጠበቅ ይገባል የሚል አቋም ይዘን ነው ያለነው"።ፍርድ ቤቱ ይህንን ጉዳይ ለመመልከት ወይም በእግዱ ላይ የተከሳሾችን ምላሽ ለማድመጥ ቀጠሮ መስጠቱን ጠበቃ አያሌው ቢታኔ ተናግረዋል።

የ2024 ኦሊምፒክ የተወዳደረዉ የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ቡድን ፓሪስ ሲገባ አቀባበል ሲደረግለት
የ2024 ኦሊምፒክ የተወዳደረዉ የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ቡድን ፓሪስ ሲገባ አቀባበል ሲደረግለትምስል Haimanot Tiruneh/DW


"ተከሳሾቹ ወይንም መልስ ሰጪዎች በጉዳዩ ላይ ሐሳብ ሊሰጡ ይገባል ብሎ ስላሰበ [ፍርድ ቤቱ] ለመስከረም ሃያ በእግዱ ዙሪያ መልሳቸውን ይዘው እንዲቀርቡ ትእዛዛት ሰጥቶበታል"።
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቲ እና አመራሮቹ ላይ ክስ ያቀረቡት አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን እንዲሁም የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን ናቸው። የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በወቅቱ  በሰጠው ምላሽ ግን "የስፖርት ነክ ጉዳዮች በመደበኛ ፍርድ ቤት እንደማይታዩ" በመግለጽ በሚደረገው ነገር "ሀገር እንዳትቀጣ" ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ሲል አሳስቦ ነበር።

ሰሎሞን ሙጬ 
ኂሩት መለሰ
ፀሐይ ጫኔ