የአማራ ክልል የአመራር ለውጥ እና የህዝቡ አስተያየት እንዲሁም የጸጥታው ይዞታ
ሰኞ፣ ነሐሴ 22 2015ማስታወቂያ
የአማራ ክልል ምክር ባሳለፍነው ሳምንት የአመራር ለውጥ ማድረጉን ይፋ አድርጓል። ክልሉ ባልተረጋጋባት በዚህ ወቅት ፕሬዝደንቱን ጨምሮ የተደረገው የአመራር ለውጥ ኅብረተሰቡ ያነሳቸውን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ እንደማይችል ዶቼ ቬለ አስተያየታቸውን የጠየቃቸው የክልሉ ነዋሪዎች አመልክተዋል። አስተያየት ሰጪዎቹ አክለውም የክልሉን ሰላም ለመመለስም በጋራ ተቀምጦ መምከር እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል። በአንጻሩ ክልሉ ምክርቤት የተደረገው ሹም ሽርን በመደገፍ የተጀመረው ወደታችኛው የአስተዳደሩ አካል ድረስ ወርዶ መፈጸም ይኖርበታል ያሉና ሂደቱን የደገፉም አሉ። ይክ በእንዲህ እንዳለም በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች በፋኖ እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ግጭት ውጊያው መቀጠሉ ይሰማል። በተለይም በደብረ ማርቆስ እና በደብረ ታቦር ከተሞች አካባቢ በተኩስ ልውውጡ ሕይወታቸውን ያጡ የየከተሞቹ ነዋሪዎችን የቀብር ሥርዓት ዛሬ መፈጸሙን ዶቼ ቬለ ካነጋገራቸው ነዋሪዎች ለመረዳት ተችሏል። በአማራ ክልል የኢንተርኔት አገልግሎት ከተቋረጠ ሳምንታት ተቆጥረዋል፤ ኅብረተሰቡ የመረጃ አማራጮችን ማግኘት እንዳልቻለ እየገለጸ ነው።
ዓለምነው መኮንን
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ