የአማራ ልዩ ኃይል «አልተበተነም» ባለስልጣን
ዓርብ፣ ሚያዝያ 6 2015
የኢትዮጵያ መንግስት የየክልሉን ልዩ ሐኃል «ዳግም ማደራጀት» ያለዉን ርምጃ በመቃወም በአማራ ክልል የተደረጉ ሰልፎች፣ አመፅና ግጭቶች በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች መርገባቸዉን የክልሉ ባለስልጣናት አስታወቁ። ለወተሮ የገለልተኛ ጋዜጠኞችን ጥያቄ የሚሸሹት የአማራ ክልል ባለስልጣናት ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።መግለጫዉን የሰጡት የክልሉ የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ቢሮ የበላይ ግዛቸዉ ሙሉነሕ እንዳሉት አብዛኞቹ የልዩ ኃይል ባልደረቦች በየተመደቡበት አካባቢ ከትተዋል።አካባቢዉንና የአባላቱን ብዛት ግን አልጠቀሱም።የልዩ ኃይል አብዛኛ አባላት «ተበትነዋል» የሚለዉን ወቀሳና አስተያየት ግን አቶ ግዛቸዉ «ሐሰት»ብለዉታል።
ባሳለፍነው ሳምንት የልዩ ኃይሉን እንደገና መደራጀት በመቃወም በበርካታ የአማራ ክልል አካባቢዎች ሞትን ያስከተሉ አለመረጋጋቶችና አመፆች ተካሂደዋል፣ ጉዳዩን አስመልክቶ የአማራ ክልል መንግስት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ዛሬ በጽ/ቤታቸው በሰጡት መግለጫ በሁሉም አካባቢዎች ያሉ ተቃውሞዎች ሙሉ በሙሉ ቆመዋል፣ ህብረተሰቡም ወደ ተለመደው ሰላማዊ ኑሮው ተመልሷል ብለዋል፡፡
“ሁሉም ቦታ ላይ የክልለላችን አካባቢዎች ወደ ነበረበት ወትሮአዊ ሰላም የተመለሰበትና በተለይ ተፈጥረው የነበሩ የመንገድ መዘጋት፣ የተሸከርካሪ መቆም፣ የንግድ ተቋማት አልፎ አልፎ የተዘገቡት ሁኔታ ነው የነበረው፣ ከህብረተሰቡ ጋር በመወያት፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋም በሰከነ መንገድ በማወያየት ጉዳዩ ተፈትቶ ማህበረሰቡ የእለት ተለት ጉዳዩን እያከናወነ ነው፡፡”
የክልሉን ልዩ ኃይሉ አዲስ አደረጃጀት በተመለከተ በተደረጉ ውይይቶች አብዛኛዎቹ የልዩ ኃይል አባላት መስማማታቸውንና ወደየተመደቡበት አካባቢ መሄድ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
“አብዛኛዎቹ የልዩ ኃይሎቻችን በተቀመጡላቸው አማራጮች የመከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የክልል መደበኛ ፖሊስ፣ የአድማ ብተናና ማረሚያ ቤቶች አካባቢ ላይ በዚህ መንገድ ስራዎች ተሰርተው ስለነበር፣ አብዛኛው ስራ ተጠናቅቋል፣ ስምሪትም ተሰጥቶ ዞን አካባቢ ብዙዎቹ ደርሰዋል፣ አቀባበልም እየተደረገላቸው ነው፡፡”
የልዩ ኃይል አባላት ተበትነው እለ እንዴት ከማን ጋር ውይይት አደረጋችሁ ተብለው በጋዜጠኞች የተጠየቁት አቶ ግዛቸው የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
“የልዩ ኃይል ዩኒፎርም የለበሰ ሁሉ ልዩ ኃል ነው ብሎ መውሰድም አይቻልም፣ ልዩ ኃይላችን አብዛኛው በአለበት ነው የጠበቀን፣ ብዙ ቦታ የነበሩ ውይይቶች ስኬታማ ነው የነበሩት፣ በሁኔታዎች በመደናገር ወደ ቤቱ የሄደ ኃይል አለ፣ ይህ ኃይል እየተመለሰ ነው ለው፣ ወደ ጫካም አልገባም ይህ ጥቂት ኃይል ነው፡፡ ”የልዩ ኃይል ጉዳይ በአማራ ክልል ያስከተለው ሕዝባዊ ቁጣ
በህልውና በህግ ማስከበር ዘመቻ ሲሳተፉ የነበሩ ሌሎች ታጣቂዎች የወደፊት እጣፋንታ ምን ሊሆን ይችላል ተብለው የተጠየቁት ኃላፊው፣ ከመንግስት ጋር በመወያየት እንደየፍላጎታቸው የሚደራጁ እንደሆነ አመልክተዋል
አንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ ጸሐፊዎች ለህብረተሰቡ የተዛባና ከእውነት የራቀ መረጃ እያሰራጩ በመሆናቸው ተጠቃሚው መዝኖና አጣርቶ የሚጠቅመውን እንዲወስድ አሳስበዋል፡፡
መንግስት በሁሉም ክልሎች ተደራጅተው የነበሩ የልዩ ኃይል አደረጃጀቶች በዋናነት ብሔር ተኮር ስለሆኑ አወቃቀራቸውም ህገመንግስታዊ ባለመሆኑ ወደ ህጋዊ መንገድ ለማስገባት አዲስ አደረጃጀት ውሳኔ መወሰኑ ይታወሳል፡፡
ዓለምነዉ መኮንን
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ