የአፍሪካ ቀንድ ወቅታዊ ሁኔታ
ሐሙስ፣ ሐምሌ 4 2016በዚህ ሳምንት የመጀመርያ ቀናት ሞቅዲሾ ከአስመራ፣ አዲስ አበባ ከካርቱም መክረዋል። ከሀገራት የተውጣጣ ሰላም አስከባሪ የሚጠብቃት ሶማሊያ የእርስ በርስ ግጭት ካልተለያት ኢትዮጵያ ጋር የገቡበት ውዝግብ አይሎ በቀጠለበት በዚህ ወቅት ፕሬዝዳንቷ በቀጣናው ሰላም ካላቸው ሀገራት አንዷ ወደሆነችው ኤርትራ ተጉዘዋል።
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር በበኩላቸው በእርስ በርስ ጦርነት ክፉኛ ወደደቀቀችው ሱዳን ተጉዘው ከሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጋር ተወያይተዋል፣ ፖርት ሱዳንንም ጎብኝተዋል።ለመሆኑ ይህ ሰሞነኛው የአካባቢው ሀገራት መሪዎች ይፋዊ ጉብኝት እና አቀባበል ምን እንደምታ አለው ? የኃያላኑ ብሔራዊ ጥቅም መሳለጫ የሆነው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሀገራት ከግጭት፣ ውዝግብ እና ጎራ ለይቶ ንትርክ መውጣት ለምን ተሳናቸው?ማሕደረ ዜና፤ የኢትዮ-ሶማሊያ ዉዝግብ፣ የአፍሪቃ ቀንድ ተጨማሪ ሥጋት
ሰሞነኛው የአፍሪካ ቀንድ ነባራዊ ሁኔታ
በተፈጥሮ ቀጣናው የሚገኝበት ስፍራ ቁልፍ ዋጋ ያለው መሆኑ፣ የሕዝቦች ነባር ፍላጎት የማይለየው መሆኑ፣ የአካባቢው ሀገራት መሪዎች ልዩ ልዩ ፍላጎት ብሎም የኃያላን እና የውጭ ሀገራት የብሔራዊ ጥቅም ፍላጎት ማራመጃ የሆነው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ከትናንት እስከዛሬ የውስብስብ ችግር መናሃሪያ የመሆኑ ምክንያት ምን ይሆን? "በመርህ ደረጃ ሀገር እና መንግሥት በሚባል ተክለ ቁመና ላይ አለመገኘታቸው ነው። ሀገር ናቸው ብንላቸውም ሀገር ግን የሚያስብል ባሕሪ የላቸውም"።
ስማቸውን ከመግለጽ ተቆጥበው ሀሳባቸውን ያካፈሉን እኒህ የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ፣ የዚህ ምክንያቱ በእርግጥም የቅኝ ግዛት ውርስ አንዱ ቢሆንም ከድኅረ ቅኝ ግዛት ዘመን በኋላ እርካብ ላይ የተቆናጠጡ መንበር ላይ የተደላደሉ የቀጣናው መሪዎች "ያበላሹት ነገር" ስለመሆኑ ያብራራሉ።"ኢትዮጵያ የነበራት ትልቅ ተደማጭነት፣ ተቀባይነት ዝቅ ስላለ የእሷን ቦታ ለመውሰድ በሀገራት መካከል መሽቀዳደም እያየን ነው"።
የበርበራ ወደብ፦ የኢትዮጵያ ወቅታዊ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴና የአፍሪቃው ቀንድ
"በዚህ ውስጥ የተሻለ በሰል ያለ መሪ ከወደ ኬንያ ተገኝቷል" የሚሉት ተንታኙ "የኤርትራው ፕሬዝዳንት በእምቢተኛነት ባህሪያቸው" መቀጠላቸውን፣ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት "ተቀባይነትና ተደማጭነት ያለው፣ ዋጋ የሚሰጠው መሪ መሆኑን እያረጋገጠ ነው" ሲሉ የሁኔታዎችን አካሄድ ያብራራሉ።
በሱዳን በኩል የሁለቱ ተፋላሚ ጀነራሎች አለመግባባት ለሌሎችም ጎረቤት ሀገራት መንግሥታትና መሪዎች ያላቸው ግምገማ ሆድና ጀርባ በመሆኑ "በአንድ በኩል ሰላም ሊመጣ አልቻለም" ሲሉ ተንታኙ ያብራራሉ። ይህ እንዳለ ሆኖ ተጻራሪ ፍላጎት ያላቸው ኢትዮጵያ እና ግብጽ ተጽእኗቸውን ለማሳደር ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ መነሻ አሁንም ለሱዳን መፍትሔ ሊገኝ አልቻለም ብለዋል።
ከሱዳን በተጨማሪ ሶማሊያና ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያቸው በተግባር ከውስጥ የመነጨ እና የሚነሳ አይመስልም የሚሉት ተንታኙ፣ መሪዎቻቸው ወደ ውስጥ ሊያተኩሩ የተገባ ስለመሆኑ ያስረዳሉ።ትኩረት በአፍሪቃ፤ የሱዳን ዉጊያ፣የአፍሪቃ ቀንድ ቀዉስ
"እነዚህ ሀገራት፤ ከኬንያ በስተቀር ወደ ውጭ የሚያተኩር የውጭ ፖሊሲ እያራመዱ እንደሆነ ፍንጭ ይሰጣል - ተግባራቸው። [ይህም] የማያዋጣ የፖሊሲ አቅጣጫ እንደሆነ ይታመንበታል"።
በዚህ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ተደማጭነቷ እያደገ የመጣው ኬንያ ሰሞነኛ ቀውስ እየለበለባት ሲሆን ትንሽ ግን ቁልፍ የሆነችው ጅቡቲ በጽማዌ በተሻለ ሰላምና መረጋጋት ወደፊት እየተራመደች ትገኛለች።
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ፀሐይ ጫኔ