የትግራይ ጡረተኞች አቤቱታቸው መልስ ማግኘት ጀመረ
ቅዳሜ፣ መጋቢት 28 2016በተደጋጋሚ የጡረታ አበላቸው እንዲከፈላቸው ሲጠይቁ ለነበሩ በትግራይ የሚገኙ ጡረተኞች የፌደራሉ መንግስት 1.6 ቢልዮን ብር መድቦ ክፍያቸውን መስጠት መጀመሩ ተገለፀ። ጡረተኞቹ የ17 ወር የጡረታ አበላቸው እንዲከፈል በተደጋጋሚ ሲጠይቁ፣ ሰላማዊ ሰልፍ ሲያደርጉ ነበር።
ሊከፈላቸው የሚገባ የ17 ወራት የጡረታ አበል እንዳላገኙ የሚገልፁ በትግራይ ያሉ ጡረተኞች፥ ክፍያቸውን እንዲሰጣቸው በሰላማዊ ሰልፍ በተደጋጋሚ ጥያቄአቸው ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
ለነዚህ በትግራይ የሚገኙ ጡረተኞች መፍትሔ መስጠቱ የሚገልፀው የመንግስት ሰራተኞች ማሕበራዊ ዋስትና አስተዳደር መንግስት 1 ነጥብ 6 ቢልዮን ብር በመመደብ የጡረተኞቹ የጦርነቱ ወቅት የ17 ወራት ክፍያቸው መስጠት መጀመሩ ይገልፃል።
በመንግስት ሰራተኞች ማሕበራዊ ዋስትና አስተዳደር የሰሜን ሪጅን ፅሕፈት ቤት ሐላፊ አቶ ተወለደ ለማ ተቋማቸው ከመንግስት ሰራተኞች መዋጫ ሳይሰበስብ የጡረታ አበል መክፈል ተቸግሮ መቆየቱ በማንሳት የፌደራሉ መንግስት ችግሩ ለመፍታት 1 ነጥብ 6 ቢልዮን ብር መልቀቁ ተከትሎ የጡረታ ክፍያው መሰጠት መጀመሩ ለዶቼቬለ ገልፀዋል።
እንደ ሐላፊው ገለፃ በትግራይ ካሉ ጡረተኞች መካከል ከ65 ሺህ በላይ የሚሆኑ ክፍያው በባንክ በኩል ይደርሳቸዋል።
በመንግስት የተከለከለ የጡረታ አበላችን ይከፈለን በማለት በተደጋጋሚ ቅሬታ ያቀርብ፣ ሰልፍ ያደርግ የነበረው የጡረተኞች ተቋሙ የመቐለ ጡረተኞች ማሕበር በበኩሉ ውዝፍ የጡረታ ክፍያው ለሁሉም ጡረተኛ ስለመድረሱ የማረጋገጥ ስራ እንደሚሰራ ገልጿል። ከተደጋጋሚ ጥያቄ በኃላ መፍትሔ መገኘቱ ጡረተኛው አስደስቷል የሚሉት የመቐለ ጡረተኞች ማሕበር ሊቀመንበሩ ዶክተር ገብረሚካኤል ንጉሰ፥ በመሰረቱ ግን መደረግ ያልነበረበት ተግባር ብለውታል።
ሚሊዮን ኃይለስላሴ
ታምራት ዲንሳ