የተዘነጋው የሱዳን ቀውስ
ዓርብ፣ የካቲት 1 2016ዓለም በዕርስ በርስ ጦርነትት እየወደመች ላለችው ሱዳን ትኩረት እንዲሰጥና ለከፋ ርሀብና ስደት የተዳረጉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሱዳናውያንን እንዲታደግ ጥሪ ቀርቧል። ለበርካታ አመታት ሱዳንን የገዙት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦማር አል ባሺር ጄርኔራሎች የነበሩት የጦር ሀይሉ አዛሽ ጄነራል አልቡርሀንና የፈጥኖ ደርሹ አዛዥ ጄነራል ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ ባለፈው ሚያዚያ ወር የእርስ በርስ ጦርነት ከጀመሩ ወዲህ በትንሹ ከ12 ሺ በላይ ሰላማዊ ሰዎች እንድተገደሉና 9 ሚሊዮን እንደተፈናቀሉ፤ ሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ ደግሞ ወደ ጎረቤት አገሮች እንደተሰደዱ የመንግስታቱ ድርጅት መረጃዎች ያሳያሉ።
የሱዳን ችግር ልዩና የከፋ የሆነባቸው ምክንያቶች
ሱዳኖች በገፍ እየተሰደዱቧቸው ናቸው የሚባሉት እንደ ቻድ፣ መካከለኛው አፍርካ ሪፑብሊክ፤ ደቡብ ሱዳንና ኢትዮጵያ የመሳሰሉት ጎረቤት አገሮችም የየራሳቸው የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና የጸጥታ ችግሮች ያሉባቸው በመሆኑ፤ ለተሰዳጅ ሱዳኖች ምቹ አይደሉም እየተባለ ነው።;።
ለጋሽ የምዕራብ መንግስታትም ቀደም ሲል በዩክሬን አሁን ደግሞ በጋዛ ቀውስ የተያዙ በመሆናቸው የሱዳንን ጉዳይ ችላ እንዳሉት እየተገለጸ ሲሆን፤ ይህ ግን ሊሆን እንደማይገባው በቅርቡ ሱዳንና ጎረቤት አገሮችን የጎበኙት የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኖች መርጃ ከፍተኛ ሀላፊ ፊሊፖ ግራንዲ ሳይቀር በግልጽ ሲናገሩ ተሰምተዋል። “ በችግር ላይ ያሉት ሱዳኖች ዓለም እንደተዋቸውና እንደረሳቸው ነው የሚሰማቸው። እርግጥ ነው ዛሬ የዩክሬንና ጋዛ ችግር አለ ፤ ለዚህም ትኩረት መስጠት ይገባል፤ ግን እኛ የሰብአዊ ድርጅቶች እየጠየቅን ያለነው፤ እለማቀፉ ማህብረሰብ ለሁሉም እጆቹን እንዲዘረጋ ነው” በማለት የሱዳንውያን ችግርም እኩል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል።
የኖርዌይ የስደተኞች መርጃ ድርጅት የሱዳን ዳይሬክተር ሚስተር ዊሊያም ካርተርም፤ የሱዳን ቀውስ ሆን ተብሎም ይሁን በሌላ ያለማቀፉን ማህብረሰብ ትኩረት ሊያገኝ እንዳልቻለ ነው የሚናገሩት፤ “በጣም የተረሳ ቀውስ ነው። ችግሩ የምግብና የጸጥታ ብቻ ሳይሆን ጠቅላላ የ50 ሚሊዮን ህዝብ አገር የሆነችው ሱዳን የመንግስትና የኢኮኖሚ መዋቅሯ በመፍረስ አደጋ ላይ መሆኑ ነው” በማለት የዕርዳታ ድርጅቶች በቂ ገንዘብ እያገኙ ባለመሆናቸው የሚፈለገውን እያደረጉ እንዳልሆነ አስታውቀዋል።
የተኩስ አቁም ጥሪ
ባሰቸጋሪ ሁኔታም ቢሆን እርዳታ ለመስጠት የሚፈልጉና እየሞክሩ ያሉ ድርጅቶችም በጦርነቱና የደህንነት ዋስትና ማጣት ምክኒያት እርዳታ ፈላጊውን ህዝብ መድረስ እለመቻላቸው ሌላውና ትልቁ ችግር መሆኑም በሰፊው ይነገራል።፡ ለተቸገረውና ከሞት አፋ ላይ ላለው ህዝብ እርዳታ ለማድረስ እንዲቻል፤ ተፋላሚ ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነት ይደርሱ ዘንድም እነዚሁ ድርጅቶች ድምጻቸውን እያሰሙ ነው። የዓለም የምግብ ድርጅት የምስራቅ ፍርካ ተጠሪ ሚኪኤል ደንፎርድ ይህንኑ ጥሪ በማስተጋባት፤ “ እየተካሄደ ባለው ጦርነትና በደህንነት ማጣት ምክንያት የተቸገሩ ሰዎችን መድረስ አልተቻለም። የተቸገሩትን ለመርዳት በቂ የገንዘብ እርዳታ ያስፈልገናል፤ ከሁሉም በላይ ግን የእርዳታ ስራችንን ለማሳለጥና የተቸገሩትን ለመድረስ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ አጥብቀን እንጠይቃለን” ብለዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ሃላፊ ሚስተር ፊሊፖ ግራንዲም በተለይ በቅርቡ ሱዳንን ከጎበኙ በኋላ ለሁለቱ ተፍላሚ ጀኔራሎች ጥሪ አስተላልፈዋል፤ “ ከዚህ ቀደም ያቀረብነውን ጥሪ በተለይ ለሁለቱ ጀኔራሎች መድገም እፈልጋለሁ። ወደ ሰላማዊ ውይይት ተመልሰው መምጣት አለባቸው። በትክክለኛው የሰላም መንገድ ላይ መራመድ ይኖርባቸዋል፤ ቢያንስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ እርዳታ ፈላጋጊዎችን ለመድረስ እንድንችል” በማለት ከቡድንና የግል ፋላጎታችው በላይ የህዝቡ ችግርና ስቃይ ግድ ሊላቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።
ለአውሮፓውያን የተሰጠ ማስጠንቀቂያና ለለጋሾች የቀረበ ጥሪ
ሚስተር ግራንዲ ለአውሮፓውያንም ማሳሰቢያ አላቸው፡ “ አውሮፓውያን የሜድትርኒያን ባህር እያቋረጡ ስለሚገቡ ሰዎች ሲጨነቁ እሰማለሁ። እኔ ግን ላሳስባቸው የምፈልገው ፤ ጦርነቱ ካልቆመ፤ ከሱዳን የተሰደደው ብቻ ሳይሆን እዚያው ተፈናቅሎ ያለውም ወደ ሊቢያና ቱኒዚያ በማምራት የሜትራኒያን ባህር ማቋረጡ የማይቀር መሆኑን ነው” በማለት አስጠንቅቀዋል።
ሰሞኑን ከመንግስቱ ድርጅት የወጣ መረጃ እንዳስታወቀው፤ በአሁኑ ወቅት ከአምሳ ሚሊዮኑ የሱዳን ህዝብ ግማሹ ወይም 25 ሚሊዮን የሚሆነው የዕለት ጉርስ የሌለው እርዳታ ጠባቂ ነው። በሱዳን ውስጥ ለተፈናቀሉትና በጎረቤት አገሮች ተጠልለው ለሚገኙ ሱዳንውያንና የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት የሚውል 4.1 ቢሊዮን ዶላር በአስቸኳይ የሚይስፈልገው መሆኑን በመግለጽም የመንግስታቱ ድርጅት ለለጋሽ አገሮች ጥሪ አቅርቧል።
ገበያው ንጉሴ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሔር
ሽዋዬ ለገሰ