የሰሞነኛው የአዲስ አበባ ጎርፍ ቢያንስ የ 14 ሰዎችን ህይወት አጠፋ
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 22 2016ሰሞነኛው የአዲስ አበባ ጎርፍ ቢያንስ የ 13 ሰዎችን ህይወት አጠፋ
ከትናንት በስቲያ እሁድ ከእኩለ ለሌት ጀምሮ በጣለው ከባድ ዝናብ አዲስ አበባ ውስጥ ቢያንስ 14 ሰዎች በጎርፍ መወሰዳቸውን የአይን እማኞች ተናገሩ። ከጎርፍ አደጋው ተርፈው አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ ሰው ህይወታቸውን በጎዳና ያደረጉ 13 ሰዎች ከአጠገባቸው መወሰዱን እና እስካሁን 8 ያህል አስከሬን መገኘቱን ተናግረዋል፡፡
ሰዒድ አሊ ይመር ይባላል፡፡ የ25 ዓመት ወጣት ነው፡፡ በዘጠን ዓመት ዕድሜው ተወልዶ ካደገበት ደሴ ከተማ የቤተሰብ ስልክ በመጣሉ ወላጆቹ ይቆጡኛል በሚል ሰበብ ከቤት እንደጠፋ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ባለፉት 16 ዓመታት የጎዳና ላይ ህይወትን የተለያዩ ሱሶች ፈተና ታክሎበት መርቷል፡፡ ከደሴ እንደመጣ ፒያሳ ጣይቱ ሆቴል አከባቢ ቢያንስ ለአምስት ዓመታት መኖሩን የሚገልጸው ወጣቱ አሁን ወደ ምገኝበት ጉርድ ሾላ ሰኣሊተምህረት ማሪያም ቤተክርስቲያን ጀርባ ባለው ጎዳና ላይ ደግሞ ላለፉት 11 ዓመታት ከትሟል፡፡ “እንዳጋጣሚ የወንድሜን ስልክ ጥዬ ነው ከቤት ወጥቼ የቀረሁት፡፡ አሁን በጎዳና ህይወት 16 ዓመት ሆነኝ፡፡ አንድ የሁለት ዓመት ልጅም አለችኝ” ይላል፡፡
የጎርፍ አደጋ የሚያሰጋቸው የአፋር፣የአማራ፣የኦሮሚያ፣የሶማሊና ደቡብ ክልሎች
ከትናንት ወዲያ እሁድ ሚያዚያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም እኩለ ለሌት ከ8፡00 ሰዓት ጀምሮ አዲስ አበባ ውስጥ በጣለው ከባድ ዝናብ ከተከሰተው የጎርፍ አደጋ በተዓምር የተረፈው ሰዒድ አጠገቡ ከነበሩት 17 ጓደኞቹ 13ቱን ደራሽ ውሃው በውድቅት ሌሊት ይዟቸው ሲሄድ በአይኑ ተመልክቷል፡፡ ከወንዙ የታችኛው ተፋሰስ ጎሮ እና ወረገኑ በሚባሉ አከባቢዎች አስከሬናቸው የተገኙ መኖራቸውን የሚያስረዳው ሰዒድ አሁን ላይ ያልተገኙ አስከሬን ፍላጋ ከጓደኞቹ ጋር ይባትላል፡፡ “ባለፈው በጣለው ከባድ ዝናብ ባጋጠመን አደጋ 5 ሰዎች ብቻ ነን ያመለጥነው፡፡ 13 ጓደኞቻችን በጎርፍ ተወስደዋል፡፡ እስካሁን ሰባቱ አስከሬናቸው ተገኝቶ ስድስቶቹን እስካሁን ፍለጋ ላይ ነን፡፡ ሶስት ሴቶች እና አንዲት የስድስት ዓመት ልጅ እንዲሁም እድሜጣቸው ከ17 እስከ 25 የሚሆኑ ዘጠን ወንዶች ከአጠገባችን ነው በዚያ ውድቅት ሌሊት የተወሰዱት” ብሏልም፡፡ ከአንድ ቦታ ከተወሰዱት 13 ሰዎች በተጨማሪ ከዚሁ ቅርብ ስፍራ ላይ ከሚገኝ ቦታም የሚያውቁት ተጨማሪ አንድ ሰው በአጠቃላይም 14 በእለቱ ጎርፉ እንደወሰዳቸውም አስረድቷል፡፡
የጎዳና ህይወት አስከፊ ገጽታ
ሰዒድ በዚሁ በጎዳና ላይ ሳለ የወለዳት የሁለት ዓመት ልጁ እና እናቷ ግን እንዳጋጣሚ ወደ ክፍላገር ቤተሰብ ጥየቃ በመሄዳቸው ከአደጋው መትረፋቸውን አስረድቷል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ጉርድ ሾላ ሰዓሊተ ምህረት ማሪያም ቤተክርስቲያን ከሚባል አከባቢ ባለው ወንዝ ድልድይ ስር ድጋይ ደርድረው ክረምትም ሆነ በጋ ማደሪያቸው አድርገው እንደሚኖሩም በመግለጽ የከትናንት በስቲያ ደራሽ ጎርፍ እጅግ ከባድ መሆን ግን ይህን ለዓመታት የኖሩበትን ስፍራ ንዶባቸው የህይወት ዋጋ እንዳስከፈላቸውም ይገልጻል፡፡ “ከውስጥ ድንጋይ ደርድረን ካርቶን አንጥፈን ነው የምንተኘው፡፡ 18ንታችንም እዚሁ ነው የምንኖረው፡፡ እንደቤተሰብ ነን” ይላልም፡፡
ታይቶ የማይታወቅ የሚለው ጎርፉ በእለቱ ስደርስ እሱን ጨምሮ አምስቶቹ እየበዛ የመጣውን ጎርፍ ፍራቻ አስቀድመው ተሻግረው ጥግ ይዘው ብቀመጡም፤ ሌሎቹ እንደወትሮው አይደርስብንም በማለት በዚያው በመቆየታቸው ጎርፉ ከከፋ በኃላ መሻገሪያ በማጣታቸው በዚያው ድቅድቅ ጭለማ በደራሹ ሲወሰዱ ከማየት ውጪ እድል እንዳልነበራቸውም ይገልጻል፡፡ “ሁሉንም አውቃቸዋለሁ፡፡ ያው በብዛት ስማቸውን እና የመጡበትን ቤተሰብ መናገር የማይፈልጉ ስላሉ አንዳዶቹ በቅጽል ስማቸው ነው የምታወቁት” ብሏልም፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎርፍ ከ3ሺህ በላይ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጭ አደረገ
ሰዒድ እና ከጎርፍ አደጋው የተረፉ ጓደኞቹ አሁን ከዚህ አደጋው ከደረሰበት ስፍራ ብለቁም ህይወት ግን በጎዳናው ቀጥሏል፡፡ ተመሳሳይ አደጋ በቀጣይስ ብከሰት ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ስሰጥም፡ “ካጋጠመም የሞሆነውን ማየት ነው እንጂ አማራጭ የለም፡፡ ነግቶ ማየታችን እንጂ ቀኑስ ምን እንደሆነ የማያውቅ እኮ ስንቱ አለ” ሲል በተስፋ መቁረጥ ስሜት አስተያየቱን ሰትቷልም፡፡
በእለቱ ስለደረሰው የአደጋ መጠንና በቀጣይም ሊደረግ ስለሚገባው ጠንቃቄ ለመጠየቅ ዶይቼ ቬለ ለአዲስ አበባ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኑኘት ኃላፊ የእጅ ስልክ ላይ በተደጋጋሚ ብደውልም ምላሻቸውን ባለማግኘታችን አስተያየታቸው ማካተት አልቻልንም፡፡ ለመንገድ ዳር ልማቱ የተቆፋፈሩ ማፋሰሻዎች ተጨማሪ የጎርፍ ስጋት ይሆን
ከተከሰተው ጎርፍ አደጋ በተጨማሪም ከሰሞኑ በመዲናዋ በተለይም ለኮሪደር ልማቱ በፈረሰባቸው አከባቢዎች ላይ የማፋሰሻዎች ችግር በማጋጠሙ አንዳንድ የከተማዋ ጎዳናዎች ለተሽከርካሪዎች የባህር ያህል ስያስቸግሩም ታይተዋል፡፡ በርግጥ በዛሬው እለት የከተማ አስተዳደሩ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር የኮሪደር ልማት ስራውን ገምግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ፍንጭ ሰጥቷል፡፡
ሥዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ