የሦስቱ አፍሪቃውያን የጀርመን ም/ቤት አባላት ማንነት
ረቡዕ፣ ሰኔ 22 2014በዚህ ዓመት በመስከረም ወር በተካሄደው የጀርመን ብሔራዊ ምርጫ አሸንፈው የጀርመን ምክር ቤት አባል የሆኑት ሦስት አፍሪቃውያን ጀርመናውያን በምክር ቤቱ የተለያዩ ኮሚቴዎች ውስጥ መስራት ጀምረዋል። አርማንድ ሶርን በዚህ ዓመት በመስከረም ወር በተካሄደው የጀርመን ሀገር አቀፍ ምርጫ አሸንፈው በጀርመን ምክር ቤት ቡንደስታግ መቀመጫ ካገኙ ሦስት አፍሪቃውያን ጀርመናውያን አንዱ ናቸው። ያውንዴ ካሜሩን የተወለዱት ሶርን ጀርመን የመጡት በ12 ዓመታቸው ነበር። የዛሬ 21 ዓመት እናታቸው አዲሱ የኑሮ አጋራቸው ወደነበሩበት ዛክሰን አንሀልት ፌደራዊ ክፍለ ግዛትዋ ሀለ ከተማ ይዘዋቸው ከመጡ በኋላ እዚያው አደጉ ተማሩም ።ሶርን ሀለ ብቻ አይደለም የኖሩት።በትምሕርት ፓሪስ ፈረንሳይ፣ ኮንስታንስ በተባለችው የጀርመን ከተማ ፣ በኢጣልያዋ ቦሎኛ ፣በስራ ደግሞ በቻይናዋ ሆንግኮንግና እና በብሪታንያዋ ኦክስፎርድም ሰርተዋል። ጀርመን ከመጡ ከ21 ዓመት በኋላ ደግሞ ብዙዎች ብጤዎቻቸው ያልደረሱበት ደረጃ ደርሰዋል። ይህ ግን እንዳለመታደል ሆነ ለብዙ ወጣቶች አይሳካም የሚሉት ሶርን ፣ይህም ዐእምሮአቸውን እረፍት የሚነሳ ጉዳይ መሆኑን ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።
«በራሴ በግሌ ፣ ጎበዝ በጣም ጠንካራ እና ብቁ ከሆኑ ወጣቶች ትልቅ ቦታ መድረስ ሲገባቸው ያልተሳካላቸው ብዙዎች እንዳሉ አውቃለሁ።ይህ ጉዳይ መቼም ሰላም ሰጥቶኝ አያውቅም።»
የዶቼቬለዋ ቤቲና ማክስ እንደዘገበችው ለመጀመሪያ ጊዜ በጀርመን ምክር ቤት መቀመጫ ያሸነፉት ሶርን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከሀለ ቪትንበርግ የማርቲን ሉተር ዩኚቨርስቲ በፖለቲካና በታሪክ ትምሕርት፣ ከፓሪሱ ሳይንስስ ፖ ተቋም በአውሮጳ ጉዳዮች ዲፕሎማ ከኮንስታንስ ዩኚቨርስቲ የማስትሬት ዲግሪ እንዲሁም ከማርቲን ሉተር ዩኒቨርስቲ በሕግ ሌላ የማስትሬት ዲግሪ አግኝተዋል። በስራው ዓለምም በቻይናዎቹ ግዛቶች በሆንግኮንግ እና በማካኦ የጀርመን የፋይናንስ ሚኒስቴር ተጠሪ ቢሮዎች ውስጥ ሰርተዋል።የካበት ዕውቀትና የስራ ልምድ ያላቸው ሶርን በጀርመን ፖለቲካ ውስጥ በንቃት መሳተፍ የጀመሩት ከጎርጎሮሳዊው 2009 ዓም አንስቶ ነው ። ከዛሬ አስራ አንድ ዓመት በፊት የአንጋፋው የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ አባል የሆኑት ሶርን በ2019 ዓም የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ጉባኤ ከፍተኛ አባል ለመሆን በቁ። ዘንድሮ መስከረም በተካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫም አሸንፈው ከዛሬ ሰባት ዓመት አንስቶ የሚኖሩበት ፍራንክፈርት ከተማ የሚገኝ ወረዳን ህዝብ በመወከል የጀርመን ምክር ቤት አባል ናቸው። በምክር ቤቱ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የፋይናንስ ኮሚቴ አባል የ33 ዓመቱን ሶርን የኮሚቴው አባል መሆናቸው ለአፍሪቃ ያለውን ጠቀሜታ አስረድተዋል።
«በፋይናንስ አካባቢ ለምሳሌ ከዓለም የፋይናንስ መረጋጋት ጋር የተያያዙ በርካታ ጉዳዮች አሉ።ጉዳዩ የተወሰኑ የአፍሪቃ ሀገራትን የእዳ ልክን ፣በተወሰኑ የአፍሪቃ ሀገራት እድገትና የኤኮኖሚ ልማትን እውን ለማድረግ በእርዳታ የሚሰጥ ገንዘብ ማቅረብን ይመለከታል።»
ሌላዋ በዚህ ዓመቱ ምርጫ የምክርቤት መቀመጫ ያሸነፉት ትውልደ ኤርትራዊቷ አወት ተስፋየሱስ ናቸው።የጀርመን ምክር ቤት አባል በመሆናቸው ከህዝብ ጋር ይበልጥ መቀራረብ መቻላቸውን ከበፊቱ ሕይወታቸ ጋር ሲያነጻጽሩት የሚሰጠውን ክብርም ለዶቼቬለ በስካይፕ ባደረጉት ቃለ ምልልስ አድንቀዋል።
«ፍጹም የተለየ ዓለም ነው። ሰዎች ሊያወያዩህ ይፈልጋሉ ግልጽ ናቸው። ሰዎችን መጋበዝ ትችላለህ ።ሆኖም በተለይ የተለያዩ የውበት መጠበቂያዎችና ተመሳሳይ ሸቀጦች መደብር ውስጥ የምትሰራ ጥቁር ሴት እቃ ትሰርቃለች አትሰርቅም ተብሎ ጥብቅ ክትትል እንደሚደረግባት አይደለም።በስልጣን ተዋረድ ከፍተኛው ቦታ ነው።ያ ትልቅ ለውጥ ነው።»
ሆኖም አወት እንደሚሉት በእለት ተእለት ሕይወታቸው ግን ዘረኝነት አልተለያቸውም። በጎርጎሮሳዊው 1974 አስመራ ለተወለዱት አወት ከዘረኝነት ጋር የተያያዘው ልምዳቸው ወደ ኃላ ይወስዳቸዋል። አወት በተወለዱበት በዚያን ዘመን ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ነበረች። በወቅቱም አገሪቱን የሚያስተዳድረው ወታደራዊ መንግሥት ነበር። አባታቸው ያኔ በፖለቲካ ንቁ ተሳታፊ ስለነበሩ አወት የ10 ዓመት ልጅ እያለች ወደ ጀርመን ተሰደዱ ።ጀርመንምጡ በርካታ ኤርትራውያን ቤተሰቦች የሚኖሩበት የስደተኞች መጠለያ አዲሱ ቤታቸው ሆነ።
«እኔ ህጻን ነበርኩ።እንደ ህጻን ሁኔታውን አቅዬ ነበር የምወስደው። ለቤተሰቦቼ ግን አስቸጋሪ ነበር። በጣም ጠባብ በሆነ በርካታ ኤርትራውያን ህጻናት በሚገኙበት ክፍል ውስጥ ነበር የምንኖረው።በአንድ ክፍል ውስጥ የኔን ቤተሰቦች ጨምሮ ስድስት ሰዎች ነበርን ።ግን እንደ ህጻን ለዚህ ዓይነቱ ነገር ትኩረት አትሰጥም።ከዚያ ይልቅ ብዙ ጥሩ ሰዎች በዚያ ስላሉ ደስተኛ ትሆናለሽ።»
ወጣትዋ አወት በጀርመን ሕግ አጥንታ የራስዋን የሕግ አገልግሎት ቢሮ ከፈተች ትኩረቱም ከስደተኞች ተገን የማግኘት መብት ጋር የተያያዘ ነበር። በስደት ወደ ጀርመን የሚመጡ ሰዎችን መርዳት ትፈልጋለች።ግን እንደፈለገችው ማድረግ አልቻለችም።በርካታ ስደተኞች በጀርመን የመኖሪያ ፈቃድ አያገኙም።በደብሊኑ ሕግ መሠረት ደግሞ ስደተኞች ተገን ለማግኘት ማመልከት የሚችሉት እግራቸው መጀመሪያ በረገጠበት የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገር ነው። አወት ስርዓቱ ያስከተለውን ይህን ችግር በፖለቲካዊ መንገድ መቀየር እንዳለብኝ ይሰማኛል ብለዋል።አወት የፖለቲካewne ዓለም የተቀላቀሉት
የዛሬ 13 ዓመት ነበr፤የጀርመን አረንጓዴዎቹ ፓርቲ አባል ሲሆኑ። በመኖሪያቸው በካስል ከተማ ለአምስት ዓመታት የምክር ቤት አባል ነበሩ።ከዚህ ዓመት ጥቅምት ወር አንስቶ ደግሞ የጀርመን ምክር ቤት አባል ናቸው። በምክር ቤቱ የባህል ኮሚቴ የፓርቲያቸው ዋና ተወካይ ሆነዋል። በዚህ ሃላፊነታቸውም የማይደረስበት የሚመስል ግብ አስቀምጠዋል፤ የተዘረፉ ባህላዊ ቅርሶች ለቅርሶቹ ባለቤት ሀገራት መመለስ አለባቸው የሚል።
«ወደ ጀርመን ቤተ መዘክሮች ስሄድ እኔ ከመጣሁበት አካባቢ የመጡ ባህላዊ እቃዎች ሳይ ልቤን ያመኛል።እዚህ የመጡት ቅርሶች በመሠረቱ ለህዝቡ ምንም ትርጉም አይሰጡም። ከዚያ ይልቅ የቅርሶቹ መገኛ ለሆኑት ሀገራት ህዝቦች ግን ብዙ ትርጉም አላቸው። ምክንያቱም የተዘረፈው ማንነታቸው ነውና»
አወትና ሶርን በዚህ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ በጀርመን ምክር ቤት መቀመጫ ያገኙ የህዝብ ተወካዮች ናቸው። ከነርሱ በተጨማሪ ከ2013 አንስቶ የቡንደስታግ አባል የሆኑት ትውልደ ሴኔጋላዊው ካራምባ ዲያቢ በዘንድሮው ምርጫ ለሶስተኛ የስራ ዘመን የምክር ቤት መቀመጫ ያሸነፉ አፍሪቃዊ ጀርመናዊ ናቸው።
«በጎርጎሮሳዊው 2013 ሁሉም ነገር አዲስ ነበር ለኔ። የመነጋገሪያ ጉዳዮችን ለማዘጋጀት ጊዜ ይወስድብኝ ነበር። መነጋገሪያ አጀንዳ ከውጭ ነበር የማገኘው።ብዙዎች የአፍሪቃ ወይም በዕለት ተዕለት የዘረኝነት ሕይወት ባለሞያ የምመስላቸው። እኔ የስነ ትምሕርትና የጥናትና ምርምር ፖለቲከና መሆኔን መገንዘብ አይፈልጉም።»
የመጀመሪያው አፍሪቃዊ የጀርመን ምክር ቤት አባል ዲያቢ በምክር ቤቱም ሆነ በመራጮቻቸው ዘንድ እውቅና የተሰጣቸው ሶሻል ዴሞክራት ፖለቲከኛ ናቸው። ዲያቢ ጀርመን የመጡት በጎርጎሮሳዊው 1980ዎቹ ነበር። በያኔው ምሥራቅ ጀርመን በሀለ ከተማ በኬምስትሪ በዶክትሬት ዲግሪ ተመርቀዋል። ዶክተር ዲያቢ ሀለን ቤቴ ቢሏትም ቀን አክራሪዎች ግን አሁንም ይህን አይቀበሉም።በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚወረወሩባቸው ዘረኛ ጥቃቶች አሁንም የዕለት ተለት ክስተቶች ናቸው። በምክር ቤት አባልነት ዘጠኝ ዓመት ያስቆጠሩት ዲያቢ የሚሰነዘርባቸው የግድያ ዛቻና መሰል ማስፈራሪያዎች ቢጎዷቸውም ዘረኛ ጥቃት ሲሰነዘርኝ ብርታቴ ህዝቡ ነው ይላሉ።
«አንድ መስመሩን የለቀቀ ዘለፋ ወይም ጥያቄ ከተለጠፈና እኔ ተቃውሞየን ካሰማሁ ድጋፋቸውን ከሚገልጹልኝ ሰዎች የሚደርሱን ግልጽ ደብዳቤዎች ፣ወይም ደግሞ ተማሪዎች በየትምህርት ቤታቸው ያሰባሰቡት ፊርማ ና ወይም በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢሜሎች ናቸው ለኔ ጥንካሪ የሚሰጡኝ ።»
ካራምባ ዲያቢ በአሁኑ የስራ ዘመን በምክር ቤቱ የውጭ ጉዳዮችና የልማት ኮሚቴ አባል ናቸው። ከ2013 ዛሬ የተሻለ የአባላት ስብጥር መኖሩን የሚናገሩት ዲያቤ ይህም በምክር ቤቱ የተለያዩ አመለካከቶች እንዲስተናገዱ ያደርጋል ብለዋል።
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ