1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እንወያይ፤ ኢትዮጵያ ሌላ ዙር ግጭትን ለመሸከም ጫንቃዉ አላት?

እሑድ፣ ሚያዝያ 20 2016

ትግራይና አማራ ክልል በሚወዛገቡባቸዉ አካባቢዎች የተቀሰቀሰዉን ዉጥረት እንዴት አያችሁት? ምንስ ተሰማችሁ? ከየትኛዉም ወገን ይሁን ያ ሁሉ ህዝብ ካለቀ እና ንብረት ከወደመ በኋላ በፕሪቶርያዉ ስምምነት ሰላም ይሰፍናል ተብሎ ሲጠነቅ ዳግም ወደ ሌላ ዉጥረት እየተገባ ነዉ? ይህን ዉጥረት ህዝቡና ሃገሪቱ መሸከም ይችላሉ? ምንድን ነዉ መደረግ ያለበት?

https://p.dw.com/p/4fGtp
አላማጣ ከተማ - ኢትዮጵያ
አላማጣ ከተማ - ኢትዮጵያ ምስል Fikru Eshsiebel

ኢትዮጵያ ሌላ ዙር ግጭትን ለመሸከም ጫንቃዉ አላት?

በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል ለሁለት  ዓመታት በተካሄደው ደም አፋሳሽ  ጦርነት በቅጡ ባላገገሙት የአማራ እና የትግራይ ክልል አዋሳኞች ዳግም ግጭት መቀስቀሱ ብዙዎችን አሳስቧል አሳዝኗልም።  የሰሜኑን ጦርነት ያስቆመዉ የፕሪቶርያ ስምምነት ተግባራዊ ተደርጎ ሰላም ያመጣል ተብሎ ሲጠበቅ ካለፈው ሚያዝያ አምስት እና ስድስት ጀምሮ በአላማጣ ከተማ ፣ በራያ አላማጣ ዛታ እና ኦፍላ ግጭት ተቀስቅሷል። በዚህ ግጭት የተፈናቀሉት ሰዎች ቁጥር ከ50 ሺህ በላይ መድረሱንም የተመድ አስታዉቋል። በሺህዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል፤ ሴቶችና ህጻናት ተፈናቃዮች የሚገኙባቸዉ ሰብዓዊ ይዞታ አሳስቦኛል ሲልም ድርጅቱ  አስታዉቋል። የተቀሰቀሰዉን ግጭት ተከትሎ  የአማራ እና የትግራይ ክልል ባለስልጣናት በየግላቸዉ ባወጡት መግለጫ አንዱ ሌላዉን ተወቃሽ አድርገዋል።  በአዲስ አበባ የሚገኙት የካናዳ ጀርመን እና የፈረንሳይ ኤንባሲዎችን ጨምሮ የቡድን ሰባት አባል ሃገራት ኤንባሲዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ "የተወሳሰቡ የፖለቲካ እና የጸጥታ ቀውሶችን ለመፍታት እና በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ሁሉንም ባለድርሻዎች ያሳተፈ ውይይት ብቸኛው መንገድ ነው ብለዋል። የፕሪቶርያዉ ስምምነት ሰላም ያመጣል ተብሎ ሲጠበቅ አሁን ዳግም የተቀሰቀሰዉ ግጭት የታየዉን የሰላም ተስፋ ያደበዘዘዉ ይመስላል። ኢትዮጵያ ሌላ ዙር ግጭት እና መፈናቀል ለመሸከም ጫንቃዉ አላት? ባላስፈላጊ ጦርነት ይህን ያህል ህዝብ ካለቀና ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰ በኋላ በሁሉም ወገኖች  አሁንም የጦርነት ነጋሪት መጎሰሙ በጤና ነው? የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግና ሙሉ ሰላም ለመፍጠር ያልተቻለው ለምንድን ነው ? 

በዚህ ዉይይት ላይ ሃሳባቸዉን እንዲያካፍሉን

ወ/ሮ ቅድስት አሳልፍ  የዓለም ዕርቅ እና ሰላም ግብረሰናይ ድርጅት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ ከአዲስ አበባ፤  

ዶ/ር ሲሳይ መንግሥቴ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌደራሊዝምና ሰብአዊ መብቶች ተመራማሪ  ከአዲስ አበባ

ዶ/ር ገብረ ኢየሱስ ተክሉ ባህታ፤ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የግጭትና ግጭት አፈታት ተመራማሪ ከመቀለ

መንግሥቱ ዳዲ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል  የፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ  ከአዲስ አበባ፤

-በትግራይ አማራ ክልል በሚወዛገቡባቸዉ አካባቢዎች የተቀሰቀሰዉን ዉጥረት እንዴት አያችሁት? ምንስ ተሰማችሁ? 
-በስምምነቱ መሰረት በሰላም መፍትሄ ይመጣል ሲባል ወደ ግጭት የተገባበት ገፊ ምክንያት ምንድን ነዉ ትላላችሁ? 

  --እንደሚታወቀዉ ሁለቱ ክልሎች ሁለት ዓመት በዘለቀዉ ጦርነት ገና አላገገሙም ፤ የፕሪቶርያዉ ስምምነት የቱ ጋ ነዉ ያለዉ በአሁኑ ወቅት ?ስምምነቱ ተግባራዊ እንዳይሆን የሚፈልጉ ሀይሎች ሊኖሩ ይችላሉ የሚሉ ወገኖች አሉ ይባላልና እናንተስ ምን ትላላችሁ?  

 --ከየትኛዉም ወገን ይሁን ያ ሁሉ ህዝብ ካለቀ እና ንብረት ከወደመ በኋላ ከሰላማዊ መፍትሄ ዉጭ ዳግም ግጭት ዉስጥ መገባቱ ችግሩ የቱ ጋር ነዉ?  ይህን ህዝቡና ሃገሪቱ መሸከም ይችላሉ? 

--እንዲህ ያሉ ግጭቶች በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እና የኑሮ ዉድነት በሚታይባት ኢትዮጵያ የሚያስከትሉት ችግሮች የታወቁና የታዩ ናቸውና ምን መደረግ አለበት ትላላችሁ? ፖለቲከኞችስ  ህዝቡን ወደ ጦርነት ሲከቱ ዝም ሊባሉ ይገባል?  ዜጎች ሚዲያዉም ጭምር በፖለቲከኞች ላይ ማሳደር ያለባቸዉ ተፅኖ ምንድን ነዉ?

ሙሉዉን ዉይይት የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ፤ አስተያየቶን ይጻፉልን! ኢትዮጵያ ሌላ ዙር ግጭት እና መፈናቀልን ለመሸከም ጫንቃዉ አላት?

አዜብ ታደሰ