በእስር ላይ የነበሩ ሰባት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራሮች ተፈቱ
ዓርብ፣ ጳጉሜን 1 2016በእስር ላይ የነበሩ ሰባት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ከፍተኛ አመራሮች ትናንት ማምሻውን 2፡00 ሰዓት ግድም ከእስር ተለቀቁ፡፡ ሰባቱ ፖለቲከኞች ከቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ የተፈቱት በዋስትና መሆኑን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ቃል አቀባይ አቶ ለሚ ገመቹ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
“ትናንት ድንገት ቤተሰብ ለጥየቃ” ሲያመሩ “ዋስ አቅርበው መውጣት ይችላሉ” መባላቸውን የገለጹት አቶ ለሚ አመሻሹን ለበርካታ ጊዜያት ከቆዩበት ቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ በዋስ ተለቀው ቤተሰቦቻቸውን መቀላቀላቸውን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል።
በኦነግ አመራሮች እስራት የሂዩማን ራይትስ ዎች ጥሪ
ትላንት ከእስር የተፈቱት አቶ አብዲ ረጋሳ፣ ሚካኤል ቦረን፣ ኬኔሳ አያና፣ ለሚ ቤኛ፣ ዶ/ር ገዳ ኦልጅራ፣ አቶ ገዳ ገቢሳ እና ዳዊት አብደታ ናቸው። አቶ አብዲ ረጋሳ እና አቶ ሚካኤል ቦረን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ነበሩ። ሌሎችም በማእከላዊ ኮሚቴ እና በፖለቲካ ኦፊሰርነት ፓርቲው ውስጥ በአመራርነት ተሳትፎ የነበራቸው ናቸው፡፡
ከአራት ዓመታት በላይ በእስር ላይ የቆዩት የፓርቲው አመራሮች በተለያዩ ጊዜያት በፍርድ ቤት ነጻ ቢባሉም በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውረው እስር ላይ መቆየታቸውን እንዲፈቱ ሲወተውቱ የቆዩ ጠበቆቻቸው እና ፓርቲያቸው በተደጋጋሚ ገልጸዋል።
ከአቶ አብዲ ረጋሳ በስተቀር ስድስቱ ፖለቲከኞች የታሰሩት ከአራት አመታት በፊት ድምጻዊ ሐጫሉ ሁንዴሳ ከተገደለ በኋላ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ ነበር። ፖለቲከኞቹ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ የተለያዩ ክሶች ቢቀርቡባቸውም ፍርድ ቤት በተለያዩ ጊዜያት በነጻ አሰናብቷቸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ኦነግ በተለያዩ ጊዜያት የፓርቲው አመራሮች “ህጋዊ ባልሆነ መንገድ” በእስር ላይ ይገኛሉ በማለት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተደጋጋሚ ውትወታ ሲያቀርብ ቆይቷል። ቦርዱም ባለፈው ግንቦት ወር ጉዳዩን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል።
የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የኢትዮጵያን 2017 አዲስ ዓመት ምክንያት በማድረግ ባለፈው ሣምንት አጋማሽ ከሶስት ሺህ በላይ የሚሆኑ የህግ ታራሚዎችን በይቅርታ መልቀቁን አስታውቋል።
ሥዩም ጌቱ
እሸቴ በቀለ