1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ዲጂታል ዓለምኢትዮጵያ

«በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት ከሰብአዊ መብት አንጻር እንዴት ይታያል?»

እሑድ፣ መስከረም 13 2016

በኢትዮጵያ ሚሊዮኖች የሚኖሩባቸው የተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከኢንተርኔቱ ዓለም እንዳይገናኙ ከተዘጋባቸው ሰነባብተዋል ። ሌላው ቀርቶ የቀጥታ ስልክ መስመር አገልግሎት የማያገኙ አካባቢዎች እና ከተሞች ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቂት የሚባሉ አይደሉም ። በኢትዮጵያ አንዳች ነገር ኮሽ ሲል የኢንተርኔት እና የስልክ አገልግሎት በተደጋጋሚ ሲቋረጥ ይስተዋላል ።

https://p.dw.com/p/4Wi9u
ዲጂታል ኢትዮጵያ 5G፤ ከኢትዮ ቴሌኮም
ዓለም በዘመኑ የደረሰበት እጅግ ፈጣኑ የ5G የኢንተርኔት ግንኙነት የሞባይል ጥቅልኢትዮጵያ ውስጥ በኢትዮ ቴሌኮም በኩል በአዲስ ዓመት ይፋ ተደርጓል ። ምስል Solomon Muchiee/DW

በእርግጥ ኢንተርኔትን መዝጋት መፍትኄ ይሆን?

በዘመነ ዳግማዊ ምንሊክ ከዋና ከተማዪቱ አዲስ አበባ ወደ ሐረር ከተማ የስልክ መስመር ሲዘረጋ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት በኢትዮጵያ «ሀ» ብሎ ጀመረ ሲል ይነበባል በኢትዮ ቴሌኮም ይፋዊ ድረገጽ። አገልግሎቱ በኢትዮጵያ ከጀመረ 129 ዓመታት አልፏል ። ከዚያን ጊዜ አንስቶም ዛሬ ዘመኑ የደረሰበት እጅግ ፈጣኑ የ5G የኢንተርኔት ግንኙነት የሞባይል ጥቅል በአዲስ አበባ መጀመሩን መንግሥት በኢትዮ ቴሌኮም በኩል በአዲስ ዓመት ይፋ አድርጓል ።

ለ2 ዓመታት በዘለቀው የትግራይ ክልል ጦርነትወቅት የኢንተርኔት አገልግሎቱ ለዓመታት ሙሉ ለሙሉ ተዘግቶ ነበር ።  በዚያው ልክ የአማራ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋን ጨምሮ ሚሊዮኖች የሚኖሩባቸው የተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከኢንተርኔቱ ዓለም እንዳይገናኙ ከተዘጋባቸው ሰነባብተዋል ። ሌላው ቀርቶ የቀጥታ ስልክ መስመር አገልግሎት የማያገኙ አካባቢዎች እና ከተሞች ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቂት የሚባሉ አይደሉም ።  

ሕዝባዊ የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪዎች ሲደረጉ፤ የፖለቲካ ውጥረት ሲነግስ፤ የፀጥታው ሁኔታ ሲደፈርስ ወይንም አንዳች ነገር ኮሽ ሲል በኢትዮጵያ የኢንተርኔት እና የስልክ አገልግሎት በተደጋጋሚ ሲቋረጥ ይስተዋላል ።  የኢንተርኔት አገልግሎቱ በተደጋጋሚ ለረዥም ጊዜያት መቋረጥ በአንድ በኩል ግጭቶች እንዳይስፋፉ ያግዛል የሚሉ የመኖራቸውን ያህል ይህ መረጃን የማግኘት መብትን መደፍለቅ እና የዕለት ተዕለት የኑሮ ዑደትን ማዛባት ነው ሲሉ ብርቱ ትችት የሚያቀርቡም አሉ ። ለመሆኑ በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት  ከሰብአዊ መብት አንጻር እንዴት ይታያል?

በውይይቱ 4 እንግዶች ተሳትፈዋል ።

  1. ይርጋ ገላው (/) አውስትራሊያ በሚገኘው የከርትን ዩንቨርስቲ መምህርና ተመራማሪ
  2. አቶ አጥናፍ ብርሃኔ፦ የመብቶች እና ዴሞክራሲ እድገት ማእከል  (CARD)ተባባሪ መስራች እና የመርኃ ግብር ኃላፊ
  3. አቶ ገረሡ ቱፋ፦ በሰላም ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራው «ኢኒሼቲቭ ፎር ቼንጅ» ተቋም መስራች ገረሱ ቱፋ
  4. አቶ ያሬድ ኃይለ ማሪያም፦ የሰብአዊ መብት ባለሞያ ናቸው ።
  5. የ5G ወይንም አምስተኛው ትውልድ የተሰኘው ፈጣኑ የኢንተርኔት መገናኛ
    የ5G ወይንም አምስተኛው ትውልድ የተሰኘው የኢንተርኔት መገናኛ እጅግ ፈጣን ከመሆኑ የተነሳ በአሁኑ ወቅት ፈጣን ከሚባለው 4G ኔትዎርክ እንኳን በፍጥነት ሲለካ 100 ጊዜ እጥፍ እንደሚበልጠው ይነገርለታል ። ምስል picture-alliance/dpa Themendienst/Z. Scheurer

በዚህ ውይይት ተሳታፊ እንዲሆኑ ለኢትዮ ቴሌኮምዋና ሥራ አስፈጻሜ ፍሬሕይወት ታምሩ በእጅ ስልካቸው በተደጋጋሚ ብንደውልም ልናገኛቸው አልቻልንም ።  በጠቅላይ ሚንሥትር ጽ/ቤትም ለሚመለከተው ክፍል የላክነው የኢሜል ግብዣ ውይይቱን እስካደረግንበት ጊዜ ድረስ ምላሽ አላገኘንም ። 

«በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት  ከሰብአዊ መብት አንጻር እንዴት ይታያል?» በሚል ያደረግነውን ሙሉ ውይይት በድምፅ ከማገናኛው ማድመጥ ይቻላል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ