በሸገር ከተማ ተጀመረ የተባለው የመምህራን የት/ቤት ምገባ
ሐሙስ፣ ጥቅምት 28 2017ከሰሞኑ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች በስፋት የተጋራው ቪዲዮ በሸገር ከተማ ውስጥ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች መምህራን ከተማሪዎቻቸው ጋር በትምህርት ቤት ምገባ ተካተው የመርሐግብሩ ተጠቃሚ ሲሆኑ ያሳያል ። የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቤቶች መምህራን ከትምህርት ቤት ትምህርት ቤት ቢለያይም የተማሪዎች እና መምህራን ምገባው መጀመሩን ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ። ምገባው ያልተጀመረበት ትምህርት ቤት መኖሩን የተናገሩም አሉ ።
የመምህራን አስተያየት
በሸገር ከተማ ውስጥ በአንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚያስተምሩና አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ ማንነታቸውን ግን ከመግለጽ የተቆጠቡ መምህር በከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቤቶች ተጀመረ ስለተባለው የመምህራን ምገባ ይህን ብለዋል፡፡ "እኔ አሁን በሸገር ከተማ ነው በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማስተምረው፡፡ እኔ በማስተምርበት ሁለተኛ ደረጃ ዘንድሮ ምገባው አልተጀመረም፡፡ ባለፈው ዓመት ግን እንዲህ በሚዲያ እንደሚወራው ሳይሆን በሳምንት ሁለት-ሶስት ቀናት እንዲሁ ደረጃው ዝቅ ያለውን ሽሮ ነገር ይሰጡን ነበር፡፡ ይህን የምልህ የአምናው ነው እንጂ ዘንድሮ ያም አልተጀመረም ተቋርጧል፡፡ እውነታው ይሄው ነው” ብለዋል፡፡
ሌላው በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚያስተምሩ አስተያየት ሰጪ መምህር ግን ስለሌላው ትምህርት ቤት ባያውቁም እሳቸው በሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት ከሰኞ እስከ ዓርብ ሁሌም ቁርስና ምሳ ለተማሪዎች እና መምህራን ለየብቻ ይቀርባል፡፡ "ከጥቅምት ወር ወዲህ በትክክል ተጀምሯል፡፡ በፊት ከ1-4ኛ ክፍል ነበር አሁን ለአንደኛ ደረጃ ትምህር ቤቶች እስከ 8ኛ ክፍል ለሁሉም መቅረብ ጀምራል፡፡ መምህራን ስታፍ አከባቢ ነው የሚመገቡት፡፡ ተማሪዎች ደግሞ መመገቢያ አዳራሽ አላቸው፡፡ ቁርስና ምሳ ነው የሚቀርበው ምንም አይልም መልካም ነው” ሲሉም ሃሳባቸውን አጋርተውናል፡፡
የሸገር ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፍራኪያ ስለመምህራን ምገባው አስተያየታቸውን አንዲሰጡን ከትላንት ጀምሮ በተደጋጋሚ የእጅ ስልካቸው ላይ ብንደውልም ስብሰባ ላይ ነኝ ብለዋል፡፡ ዛሬም ደጋግመን ብንደውልላቸውም ፈቃደኝነታቸውን አላገኘንም፡፡
የምገባ አስተዋጽኦ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስርዓተ ትምህርት መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሀምቢሳ ቀነዓ የተማሪና መምህራን ምገባው በአዎንታዊ የሚታይ ተግባርነቱ ለጥያቄ የማይርብ ቢሆንም ጉዳዩ ስነልቦናዊ ግጭት እንዳይፈጥር መጠንቀቅ ያስፈልጋል ነው ይላሉ፡፡
"የተማሪ ምገባ የትም አለ በአውሮጳ ልምዱን ዐውቀዋለሁ” የሚሉት ባለሙያው መምህራን ከተማሪዎቻቸው ጋር ስመገቡ የመምህራን ተማሪዎች ህብረት በማጠናከር ለትምህርት ጥራቱም አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ እናም መምህራን ከተማሪዎቻቸው ጋር ቢመገቡ የሚገርም አይደለም፡፡ ግን ይህ ጉዳይ ዜና የሚሆንበት መንገድ በተለይም መምህራንን መገብን በሚል ከስነልቦናቸው ጋር በሚጋጭ መልኩ ማቅረብ ግን መልካም አይደለም ሲሉም አክለዋል ።
የመምህራን የኑሮ መሻሻል ጥያቄ
የትምህረት ባለሙያው ፕሮፈሰር ሀምቢሳ አክለውም "ዞሮ ዞሮ ነገሩ የመምህራን የሕይወት ደረጃ የት እናዳለ የሚያሳይ ክስተት ነው፡፡ ሰው ሞኝ ሆኖ እንጂ መምህራን ሳይከበሩ የሚገባቸውንም ክብር ሳያገኙ ስለነገያችን ተስፋ የሚጣልበት የነገ ትውልድ ማሰብ ይከብዳል፡፡ ዜና መሆን የነበረበትም መግበናል ሳይሆን ሕይወታቸውን በተጨባች የሚያሻሽል ነገር ማድረግ ነበር” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዝዳንት ዮሓንስ በንቲ በፊናቸው፤ "የመምህራን ደመወዝ እንዲሻሻል ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ ጥናቶችን አቅርበናል፡፡ አሁን ኑሮ እየጨመረ ሲሄድ ይበልጥ ሕይወታቸው እየተዳከመ መጥቷል፡፡ በዚህ ላይ ምንግስት አይቶ መፍትሄ እንዲሰጥበት በጉባኤም ተወያይተን እየጠየቅን ነውና ከእኛ የቀረ የለም”ብለዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ