1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለሰላም ስምምነቱ የአፍሪቃ ኅብረት የተጫወተው ሚና

ዓርብ፣ ጥቅምት 25 2015

ዛሬ ሁለት ዓመታት የሞላውን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፋላሚዎቹ የኢትዮጵያ መንግስት እና ሕወሓት ውጊያ ለማቆም ተስማምተው ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በፊርማ አጽድቀዋል። በደካማነት ወቀሳ እና ትችት የማይለየው የአፍሪካ ሕብረት ይህንን ተግባር በመምራት እና በማስተናበር የወሰደው ኃላፊነት በምን ደረጃ የሚታይ ነው ?

https://p.dw.com/p/4J5na
Pretoria | Waffenstillstandsabkommen für Äthiopien
ምስል Themba Hadebe/AP/picture alliance

ለሰላም ስምምነቱ የአፍሪቃ ኅብረት የተጫወተው ሚና

ሰሜን ኢትዮጵያ ላይ ተቀስቅሶ በውል የጉዳቱ መጠን ያልታወቀ ሰብዓዊ እና የቁስ ውድመት ያደረሰው የእርስ በርስ ጦርነት ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ተኩስ ለማቆም ስምምነት በማድረግ እርቅ ማውረዳቸውን አሳውቀዋል። ይህንን ሥራ በበላይነት የመራውና ያስተባበረው የአፍሪካ ሕብረት ፣ተፋላሚ ኃይሎች ስምምነቱን በፍጥነትና በቁርጠኝነት እንዲተገብሩ አሳስቧል። ለመሆኑ ይህ የተኩስ ማቆም የሰላም ስምምነት እንዲደረስ የአፍሪካ ሕብረት የተወጣው ኃላፊነት እንዴት ይገለጣል ? በከፍተኛ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚያስተምሩ ሁለት የአለምአቀፍ ግንኙነት መምህራንን ምልከታቸውን ጠይቀናል።

ዛሬ ሁለት ዓመታት የሞላውን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፋላሚዎቹ የኢትዮጵያ መንግስት እና ሕወሓት ውጊያ ለማቆም ተስማምተው ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በፊርማ አጽድቀዋል።
በደካማነት ወቀሳ እና ትችት የማይለየው የአፍሪካ ሕብረት ይህንን ተግባር በመምራት እና በማስተናበር የወሰደው ኃላፊነት በምን ደረጃ የሚታይ ነው ? 
ዶክተር ታዬ ብርሃኑ የአለምአቀፍ ግንኙነት መምህር ናቸው። 

"አፍሪካ እንደ ሕብረት ራሱ ምን ያህል ጠንካራ ነው ? ምን ያህል ተጠናክሮ ሥራዎችን ያካሂዳል ? የሚለው በጥያቄ ላይ ያለ ነው። ይሁንና የኢትዮጵያን ጉዳይ በመከታተል ፣ በመምራት ለፍፃሜ ማብቃቱ አንድ ጥሩ ውጤት ነው ማለት ይቻላል። ይህንን ስላደረገ ሚናው ተጠናክሯል ጎልብቷል ለማለት ሳይሆን ጅምሩ እሰይ የሚያሰኝ ነው" ብለዋል። 

Symbolbild African Union | Mahamat Moussa Faki
ሙሳ ፋኪምስል John Thys/AFP

ሌላኛው የአለምአቀፍ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ መምህር ዶክተር ሳሙኤል ተረፈ "ከውጪ መንግሥታት፣ ከተባበሩት መንግሥታት፣ ከአውሮፓ ሕብረት የፌዴራል መንግስቱ ላይ ጫና የማሳደር አካሄዶች ነበሩ። በዚህ ምክንያት ችግሩ በቀላሉ በሰላም እንዲፈታ የሚደረጉ ጥረቶች የተሳካ እንዳይሆኑ ሲያደርግ ቆይቷል። የአፍሪካ ሕብረት አጠር ባለ ጊዜ ይህንን ማድረጉ ችግሩ እንዲፈታ አንድ እርምጃ እንዲሄድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። 

"ትልቅ እመርታ ያለው የግጭት አፈታት ሥርዓትን፣ ተምሳሌታዊ መሆን የሚችል እንደ ማሳያና ማስተማሪያነት መውጣት የሚችል ይሆናል። የቀረቡት የድርድሩ አመቻቾችም ይህንን ልምዳቸውንና ክህሎታቸውን ተጠቅመው ሌሎች በአፍሪካ በተመሳሳይ ችግር ውስጥ የሚገኙ ሀገሮችና መንግሥታትን የውስጥ የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ሥራዎችን እንደማበረታቻነት ለመሥራት ምሳሌ ይሄናል ብዬ አስባለሁ" ብለዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ያስከተለው ውጊያ እንዲቆም ተዋጊዎቹ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ማስቻሉ የሚያስመሰግነው ቢሆንም ፣ ውጤቱ በሂደት የሚታይ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ታዬ ሕብረቱ በራሱ ራሱን ችሎ ሊቆም ገና ብዙ የሚቀረው መሆኑን ግን አልሸሸጉም።
"ሁልጊዜ በአንድ ሀገር ውስጥ ለሚፈጠሩ ችግሮች ሕብረቱ ይግባ የሚለው አካሄድ ብዙ የሚያስኬድም አይደለም፣ አቅሙም አይኖረውም። ይህ አንድ ትልቅ ጅምር ነው። ራሱ አፍሪካ ሕብረት ገና መጠናከር ይኖርበታል" 
ግጭት አፈታት ቀላል እንዳልሆነና ብዙ ምልልስ እንደሚጠይቅ የሚናገሩት ዶክተር ሳሙኤል የሕብረቱ የሰላምና ደህንነት መዋቅር ከፍተኛ የሆነ ቋሚ መሰረት ያለው የገንዘብ ድጋፍ ችግር ውስጥ የወደቀ ነው። በአህጉሩ የቅድመ ግጭት ማስጠንቀቂያ ሥራ ላይም ጠንካራ ሥራ ሲሰራ አይታይም ብለዋል።
የተፈረመው ስምምነት በፍጥነት ተግባራዊ ተደርጎ የሕዝቦች ሰቆቃ መቆም የሚችልበት ቀርጠኝነት ከፊት የሚጠብቅ ቁልፍ ሥራ መሆኑንም አብራርተዋል።
የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 ብሎ ከነደፋቸው እቅዶች መካከል የአህጉሩን ችግሮች በአፍሪካዊያን መፍታት የሚለው አንደኛው ግቡ ነው።

 

ሰሎሞን ሙጬ

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ